እስልምና እና ሽብርተኝነት
ማርክ ኤ. ገብርኤል
ቅንብር በአዘጋጁ

ምዕራፍ ሁለት

የግብፅ ወኅኒ ቤት

 

ከግብፅ ህቡዕ ፖሊስ ጋር ጊዜን ማሳለፍ የአሜሪካን እስር ቤት ከመጎብኘት የተለየ ነው፡፡ የሽብር ተግባርን በመፈጸም ከተከሰሱ ሁለት አክራሪ ሙስሊሞች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ፡፡ አንዱ ፍልስጥኤማዊ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ግብፃዊ ነበር፡፡

ለሦስት ቀናት ያህል እህልም ሆነ ውሃ አልተሰጠኝም ነበር፡፡

 

በየዕለቱ ግብፃዊው ሰው “ለምን እዚህ መጣህ?” በማለት ይጠይቀኝ ነበር፡፡ እኔም እስልምናን መጠራጠሬን ካወቀ ይገድለኛል ብዬ ስለፈራሁኝ ለመመለስ ፍቃደኛ አልሆንኩለትም፡፡ በሦስተኛው ቀን ላይ ግን በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በጊዛ መስጊድ ደግሞ ኢማም መሆኔን አወጋሁት፡፡ ወድያውኑ ውሃ በፕላስቲክ እና ጠያቂዎቹ ያመጡለትን ፋላፌል (ከሽምብራ የሚሰራ የመካከለኛው ምስራቅ የባሕል ምግብ) እና ቂጣ ሰጠኝ ነገር ግን ምንም ነገር እንዳይሰጠኝ ፖሊሶች አስጠንቅቀውት እንደነበር ነገረኝ፡፡

 

በሦስተኛው ቀን ምርመራ ተጀመረ፡፡ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት የህቡዕ ፖሊስ ግብ እኔ እስልምናን መልቀቄን ማሳመን እና ያም ደግሞ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ማውጣጣት ነበር፡፡

 

ምርመራው የተጀመረው ትልቅ ጠረጴዛ ባለበት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ እኔና መርማሪው በጠረጴዛው ወዲያ እና ወዲህ በትይዩ ተቀመጥን፡፡ ከእኔ በስተጀርባ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ፖሊሶች ነበሩ፡፡

 

እኔ ወንጌል እንደተመሰከረልኝ እና ወደ ክርስትና እንደተለወጥኩኝ እርግጠኞች ስለነበሩ “ያናገርከው ፓስተር ማን ነበር? ወደ የትኛው ቤት ክርስቲያን ነበር ስትሄድ የነበረው? ለምንድነው እስልምናን የካድከው?” በማለት በተደጋጋሚ ይጠይቀኝ ነበር፡፡

 

ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ፡፡ አንድ ጊዜ መልስ ለመስጠት ብዙ አቅማማሁ፡፡ ከጀርባዬ የነበሩትን ሰዎች  ጠቀሳቸው፡፡ እጄን በመጠምዘዝ ጠረጴዛው ላይ አጣብቀው ያዙኝ፡፡ መርማሪዬ በእጁ ላይ ይዞት የነበረውን የተለኮሰ ሲጋራ እጄ ላይ ተረኮሰው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ይህ ጠባሳ በእጄ ላይ አለ፡፡ ተመሳሳይ ነገር ስላደረገብኝ በከንፈሬም ላይ ጠባሳ አለኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲናደድ ሲጋራውን ይጠቀም ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖሊሶቹ ፊቴ ላይ ይመቱኝ ነበር፡፡

 

ምርመራው በቀጠለ ቁጥር ተፅዕኖውም ከፍ እያለ መጣ፡፡ አንድ ጊዜ የእሳት መቆስቆሻ ብረት ወደ ክፍሉ ይዘው መጡ፡፡ በውስጤ ለምን ይሆን? በማለት ተደነቅሁኝ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ መርማሪው መናገር ሲጀምር ለምን እንደሆነ ገባኝ፡፡ መቆስቆሻው ግሎ ቀይ ከሆነ በኋላ አንዱ ፖሊስ በግራ እጄ ስጋ ውስጥ ሰደደው፡፡

 

እኔ መለወጤን እንድናዘዝ ነበር የፈለጉት ነገር ግን እኔ እንዲህ አልኳቸው፡ “እኔ እስልምናን አልካድኩም፡፡ የማምነውን ብቻ ነው የተናገርኩት፡፡ እኔ የትምህርት ሰው ነኝ፡፡ እኔ አሳቢ ነኝ፡፡ የእስልምናን የትኛውንም ርዕሰ ጉዳይ የመወያየት መብት አለኝ፡፡ ይህ ስራዬ እና የየትኛውም የትምህርት ሕይወት አካል ነው፡፡ እስልምናን ለመተው አልሜ እንኳ አላውቅም፡፡ ደሜ ነው፣ ባህሌ ነው፣ ቋንቋዬ ነው፣ ቤተ ሰቤ ነው፣ ሕይወቴም ነው፡፡ ስለተናገርኳችሁ ነገሮች እስልምናን ትተሃል በማለት የምትወነጅሉኝ ከሆነ ከእስልምና አውጡኝ፡፡ ከእስልምና ውጪ ብሆን ቅር አይለኝም፡፡”

 

ግርፋቱ

 

መልሴ እነርሱ ሊሰሙት የፈለጉትን ዓይነት አልነበረም፡፡ የብረት አልጋ ወደ ነበረበት ክፍል ተወሰድኩኝ፡፡ እግሮቼን በአልጋው እግሮች ላይ በማሰር ወፈር ያሉ ገምባሌዎችን አጠለቁልኝ፡፡

 

አንዱ ፖሊስ  አራት ጫማ ያህል የሚረዝም ጥቁር አለንጋ ይዞ ነበር፣ ይገርፈኝም ጀመረ፡፡ ሌላው ፖሊስ ትራስ በእጁ በመያዝ በአልጋው ፊት ከአጠገቤ ቆመ፡፡ እኔ ስጮኽ ድምፄ እስኪጠፋ ድረስ ትራሱን ፊቴ ላይ አጥብቆ ይይዝ ነበር፡፡ እኔ ጩኸቴን ባለማቆሜ ሁለተኛው ፖሊስ ተጨማሪ ትራስ ፊቴ ላይ ለማድረግ መጣ፡፡

 

ስገረፍ ሳለሁኝም እራሴን ሳትኩኝ ነገር ግን ስነቃ አሁንም ድረስ ፖሊሱ እግሮቼን ይገርፍ ነበር፡፡ ከዚያም ግርፋቱን ጋብ በማድረግ ፈቱኝ፤ አንዱ ፖሊስም “ተነስና ቁም” በማለት አዘዘኝ፡፡ መጀመርያ ላይ አልቻልኩኝም ነበር ነገር ግን እኔ እስክቆም ድረስ  አለንጋውን በማንሳት ጀርባዬን ይገርፈኝ ነበር፡፡

 

ከዚያም ረጅም መተላለፍያን በማሳየት “እሩጥ” አለኝ፡፡ አሁንም መሮጥ ሲያቅተኝ መተላለፊያውን ሮጬ ወደታች እስክወርድ ድረስ ጀርባዬን ይገርፈኝ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ስደርስ ሌላ ፖሊስ ቆሞ ይጠብቀኝ ነበር፡፡ ወደ መጣሁበት በሩጫ እስክመለስ ድረስ እርሱም ይገርፈኝ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ በሩጫ አመላለሱኝ፡፡

 

ኋላ ላይ ለምን ያንን እንዳደረጉ ገባኝ፡፡ ሩጫው እግሬ እንዳያብጥ የታሰበ ነበር፡፡ ገምባሌዎቹ የተደረጉበት ምክንያት ደግሞ ከግርፋቱ የተነሳ እግሬ ላይ ምልክት እንዳይኖር ነበር፡፡ ትራሶቹ ደግሞ ማንም ስጮኽ ድምፄን እንዳይሰማ የታሰበ ይመስለኛል፡፡

 

ከዚያም ከመሬት ከፍ ያለ አነስተኛ የመዋኛ ገንዳ ወደሚመስል ነገር ተወሰድኩኝ፡፡ ቀዝቃዛ በሆነ በረዷማ ውሃ የተሞላ ነበር፡፡ አለንጋውን የያዘው ፖሊስ “ግባ” አለኝ፤ እኔም ገባሁኝ፡፡ በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ ለመውጣት እፍጨረጨር ነበር ነገር ግን ለመውጣት በሞከርኩን ቁጥር እየገረፈ ይመልሰኝ ነበር፡፡

 

ዝቅተኛ የደም ስኳር ስለነበረብኝ ራሴን ለመሳት ጊዜ አልፈጀብኝም ነበር፡፡ ስነቃ ከነእርትብ ልብሴ መጀመርያ እግሮቼን የተገረፍኩበት አልጋ ላይ ተኝቼ ነበር፡፡ 

 

አንድ ሌሊት በጭለማ ውስጥ

 

አንድ ምሽት ከሕንፃው በስተጀርባ ተወሰድኩኝ፡፡ ምንም መስኮት እና በር የሌላት አነስተኛ የግንብ ክፍል ተመለከትኩኝ፡፡ የነበራት ክፍተት በጣርያዋ በኩል ያለው ብርሃን መግቢያ ብቻ ነበር፡፡ መሰላል በማምጣት ወደ ላይ እንድወጣ ካደረጉ በኋላ “ግባ” የሚል ትዕዛዝ ሰጡኝ፡፡ ጠርዙ ላይ ተቀምጬ እግሮቼን ክፍተቱ መሃል ሳደርግ ውኃ ነካሁ፡፡ የሆነ ነገርም ውኃው ላይ እየዋኘ እንደሆነ ማየት እችል ነበር፡፡ ይህ መቀበርያዬ ነው፤ በቃ ዛሬ ሊገድሉኝ ነው በማለት አሰብኩኝ፡፡

 

ወደ ክፍተቱ ውስጥ ስገባ ውኃው ሰውነቴን በመሸፈን ወደ ላይ ሲወጣ ተሰማኝ፡፡ ከዚያም በእግሬ ጠንካራ መሬት ስነካ ገረመኝ፡፡ ውኃው እስከ ትከሻዬ ድረስ ብቻ ነበር የደረሰው፡፡ ከዚያም ሲዋኙ ያየኋቸው አይጦች በፊቴ እና በጭንቅላቴ ላይ ሁሉ መርመስመስ ጀመሩ፡፡ አይጦቹ ለረጅም ጊዜ ምግብ አልተሰጣቸውም ነበር፡፡ መርማሪዎቼ ብልጦች እየሆኑ ነበር፡፡ “ይህ ሰው  አሳቢ ሙስሊም ነው ስለዚህም አይጦች ጭንቅላቱን እንዲበሉት እናደርጋለን” አሉ፡፡

 

የብርሃን መግቢያን ከዘጉ በኋላ የመጀመርያውን ደቂቃ በታላቅ ፍርሃት ነበር ያሳለፍኩት፡፡ ሌሊቱን በሙሉ እዚያ በመተው ጠዋት ላይ በሕይወት መኖሬን ለማረጋገጥ ተመልሰው መጡ፡፡ የብርሃን መግቢያው ተከፍቶ ብርሃን ሳይ ለመትረፌ እና በሕይወት ለመኖሬ ተስፋን ፈነጠቀልኝ፡፡

 

ሌሊቱን በሙሉ አንድም አይጥ ሳይነክሰኝ አደርኩኝ፡፡ ጭንቅላቴ ላይ በመውጣት ፀጉሬ ውስጥ ገብተው ነበር፣ ጆሮዬንም ሲነካኩት ነበር፡፡ አንዲት አይጥ ትከሻዬ ላይ ቆማ ነበር፡፡ አፋቸው ፊቴን ሲነካካ ይሰማኝ ነበር ነገር ግን የመሳም ያህል ነበር፡፡ ጥርስ የሚባል ነገር አልተሰማኝም ነበር፡፡ አይጦቹ በሚገርም ሁኔታ ታማኞች ሆነውልኝ ነበር፡፡ ዛሬ እንኳ አይጥ ሳይ የአክብሮት ስሜት ይሰማኛል፡፡ አይጦቹ እንደዛ አይነት ጠባይ ለምን እንዳሳዩ አሁንም ድረስ ሊገባኝ አልቻለም፡፡

 

ከውድ ጓደኛዬ ጋር ተገናኘሁ

 

ምርመራው ገና አላለቀም ነበር፡፡ በኋላም ፖሊሶቹ ወደ አንዲት ጠባብ ክፍል በር በመውሰድ “አንድ በጣም የሚወድህ እና ሊያይህ የሚፈልግ ሰው አለ” አሉኝ፡፡ “ማነው እርሱ?” በማለት ጠየቅኋቸው፡፡ ከቤተ ሰቦቼ መካከል አንዱ ወይንም ሊያየኝ እና ሊያስፈታኝ የመጣ ወዳጄ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩኝ፡፡

 

“አንተ አታውቀውም እርሱ ግን ያውቅሃል” በማለት መለሱልኝ፡፡ የከፍሉን በር ሲከፍቱ ትልቅ ውሻ አየሁኝ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ሁለት ሰዎች እኔን ወደ ውስጥ በማስገባት በሩን ዘግተውብኝ ሄዱ፡፡

 

ይህ ልቤ የጮኸበት የመጀመርያው ጊዜ ነበር፡፡ በልቤ ውስጥ ወደ ፈጣሪዬ ጮኽኩኝ፡፡ አንተ አባቴ ነህ አምላኬም ነህ፡፡ አንተ ትጠብቀኛለህ፡፡ በነዚህ ክፉዎች እጅ እንዴት ትተወኛለህ? እነዚህ ሰዎች ምን ሊያደርጉብኝ እየሞከሩ እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን አንተ ከእኔ ጋር እንደምትሆን አውቃለሁ፡፡ አንድ ቀንም አይሃለሁ፣ ከአንተም ጋር እገናኛለሁ፡፡

 

ወደ ባዶ ክፍሉ መሃል ላይ በመሄድ እግሬን በማጠላለፍ ቀስ ብዬ ወለሉ ላይ ተቀመጥኩኝ፡፡ ውሻው በመምጣት ከፊት ለፊቴ ተቀመጠ፡፡ ይህ ውሻ ዝም ብሎ ሲመለከተኝ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ አይኖቹ በተደጋጋሚ ከላይ ወደ ታች ሲንቀሳቀሱ አይ ነበር፡፡ ገና ወዳላወቅሁት አምላክ በልቤ ውስጥ መፀለይ ጀመርኩኝ፡፡

 

የሆነ ነገር ሊበላ እንዳለ እንስሳ ውሻው በመነሳት ዙርያዬን ይዞር ጀመር፡፡ ከዚያም በስተቀኜ በኩል በመምጣት ጆሮዬን በምላሱ መላስ ጀመረ፡፡ በስተቀኜ በመቀመጥ እዚያው ቆየ፡፡ በጣም ደክሞኝ ነበር፡፡ እርሱ እዚያ በተቀመጠ ጊዜ ወድያውኑ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ፡፡

 

ስነቃ ውሻው በቤቱ ጥግ ላይ ነበር፡፡ ደህና አደርክ? እንደማለት ወደ እኔ ሮጦ መጣ፡፡ የቀኝ ጆሮዬን ደግሞ በመላስ አሁንም በስተቀኜ ተቀመጠ፡፡

 

ፖሊሶቹ በሩን ሲከፍቱ ውሻው ከአጠገቤ ተቀምጦ ስፀልይ ተመለከቱኝ፡፡ ከመካከላቸው አንዱም “ይህ ሰውዬ ሰው መሆኑን ማመን አልችልም፡፡ ይህ ሰውዬ ዲያብሎስ ነው፤ ሰይጣን ነው፡፡” ሌላኛው ደግሞ “እኔ እንደዚያ አላምንም፡፡ ከዚህ ሰውዬ በስተጀርባ ቆሞ እየጠበቀው ያለ የማይታይ ኃይል አለ” በማለት መለሰ፡፡ “የትኛው ኃይል? ይህ ሰው ከሃዲ ነው፡፡ ይህ ሰው የአላህ ተቃዋሚ ስለሆነ የሰይጣን ኃይል መሆን አለበት፡፡”

 

የሆነ ሰው ጥበቃ ሲያደርግልኝ ነበር

 

ወደ ክፍሌ መልሰው ወሰዱኝ፡፡ እኔ እዝያ ባልነበርኩበት ጊዜ ክፍሌን ይጋራ የነበረው ሰው “ለምንድነው ይህንን ሰው የምታሰቃዩት?” በማለት አንዱን ፖሊስ ጠይቆት ነበር፡፡

 

“እስልምናን እየካደ ስለሆነ ነው” በማለት መለሱለት፡፡ ያም የክፍል ተጋሪዬን ቁጣ እንዲነድበት አደረገ፡፡ ወደ ክፍሉ ተመልሼ በገባሁበት ጊዜ ሊገድለኝ ዝግጁ ነበር፡፡ እኔ በክፍሉ ውስጥ ገና ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ደቂቃ ሲሆነኝ አንድ ፖሊስ የዝውውር ወረቀት ይዞ በመምጣት ወስዶት ሄደ፡፡

 

እንዲህም ብዬ ራሴን ጠየቅሁት፡ ምንድነው እየሆነ ያለው? ምን ዓይነትስ ኃይል ነው እየጠበቀኝ ያለው? በወቅቱ መልሱ ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር፡፡

 

ስለ እርሱ ብዙም በመጨነቅ ጊዜ አላጠፋሁም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የእኔም የዝውውር ወረቀት መጣ፡፡ በደቡባዊ ካይሮ ወደሚገኝ መደበኛ ወኅኒ ቤት ተወሰድኩኝ፡፡

 

በዚህ ጊዜ መርማሪዎቼ የሰው ፍጥረቶች መሆናቸውን ማመን ከብዶኝ ነበር፡፡ እስልምናን ስለተጠራጠርኩኝ ብቻ ነበር የተያዝኩት፡፡ አሁን ግን እምነቴ በትክክል ተናግቷል፡፡ ወደ ሌላ ወኅኒ ቤት እየተዛወርኩኝ ነበር፡፡

 

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ

 

በግብፅ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረውና ታዋቂው ምሁር እስልምናን በመጠራጠሩ ብቻ በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ ስቃዮችን በጥቂት ገፆች አስፍሮልናል፡፡ ያነበብነውና ጸሐፊው የተሰቃየው ከፍተኛ ስቃይ የተገለፀው ጸሐፊው የመጻፍ ችሎታ ስለነበረው እንዲሁም የሚጽፍበት ነፃነትን እግዚአብሔር ስላስገኘለት ነው፡፡ ከዚህ እጅግ በጣም የባሱና አሰቃቂ ሁኔታዎች የሚያጋጥማቸው ስንቶች ናቸው? ስንቶች ናቸው ከቤተሰቦቻቸው ተወስደው እራሳቸው የተቆረጠው? ስንቶች ናቸው ከነቤተሰቦቻቸው በፈንጂ የነደዱት?

 

በእስልምና እምነት ተመሳሳይ አመለካከትና ሌሎች እምነቱን መከተል አለባቸው የሚል የማስገደድ አመለካከት መሰረት ከፍተኛ ስቃይ የተሰቃዩትን ሰዎች መቁጠርም መገመትም አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ ቅንነት የሞላው አዕምሮ ያላቸው ሙስሊሞች ሁሉ ይህ የሚሆነው ለምንድነው? የሚል ጥያቄን በግልፅነት መጠየቅ እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ በእርግጥ ሰዎችን ማሰቃየትና መግደል የፈጣሪ ትዕዛዝ ሊሆን ይችላልን? ከሆነ ለምን ሌሎች እምነቶች ተመሳሳይ ሁኔታ አሁን አይታይባቸውም?  መልሱን ዓለማችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ለሚከታተሉ እና ሰብዓዊ ርህራሄ ላላቸው ሁሉ እንተወዋለን፡፡

 

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ክርስትያኖች ነን፣ ለሙስሊሞችና ለሌሎች እምነት ተከታዮች እውነተኛ ፍቅር ያለውን አምላክ የሰማይና የምድር ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እናመልካለን፡፡ ሌሎች ሰዎች የተለየ እምነት ስላላቸው እነርሱን የምንጠላበት፣ የምናሳድድበት፣ የምናሰቃይበት ትዕዛዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ አልተሰጠንም፡፡

 

እኛ የታዘዝነው ጠላቶቻችንን እንድንወድ፣ የዘላለም ሕይወት ማለትም መንግስተ ሰማይ የመግባት የእግዚአብሔር ይቅርታ የሚገኘው አሁን በዚህ ምድር እያለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ በክርስቶስ የታረቅን ከሆነ ብቻ እንደሆነ እንድናውጅ ነው፡፡ ይህንንም እውነት ለሰዎች ካቀረብን በኋላ ውሳኔውን የምንተወው ለሰዎች ለራሳቸው ነው ሰዎችን አናስገድድም፣ ማስገደድም የለብንም፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ የወደደውን እምነት ሊከተል መብትና ነፃነት ሊኖረው እንጂ በእኛ የግድ ሊባል አይገባውም፡፡

 

በዚህ ድረ-ገፅ ላይ የምናቀርባቸው ሃሳቦችም በሙሉ የሚያንፀባርቁት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በግልፅና በትኩረት አስተውለው የእግዚአብሔርን ምህረት በክርስቶስ በአዳኙ በኩል እንዲቀበሉ ነው፡፡ አንባቢ ሆይ እባክህ መጽሐፍ ቅዱስን ፈልግና አንብብ፣ ለዘላለማዊ ነፍስህ ምግብ፣ ለዘላለማዊዋ ነፍስህ ዘላለማዊ ምሪትን ይሰጥሃል፣ እግዚአብሔር ይርዳህ!!

 

ወደ ማውጫው መመለሻ

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ