እስልምና እና ሽብርተኝነት
ማርክ ኤ. ገብርኤል
ቅንብር በአዘጋጁ


መቅድም

መስከረም 11, 2001 በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ውስጥ እግዚአብሔር ጎላ ባለ እና ግልፅ በሆነ ሁኔታ እየተናገረ ያለው የሆነ ነገር አለ፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች በዚህች ፕላኔት ላይ አሉን፤ እናም የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን እምነታችንን ለነዚህ ሰዎች በማድረስ ምላሽን መስጠት ግድ ይላታል፡፡

ችግሩ ግን ሙስሊሞች ምን እንደሚያምኑ እና ስለ ማንነታቸው ያለን ግንዛቤ በጣም ውሱን መሆኑ ነው፡፡ ቴሌቪዥናችሁን በምትከፍቱበት ጊዜ ቤተሰብን በተመለከተ ያለው እሴት በጣም ጥሩ ስለሆነ እስልምና ለአሜሪካ መልስ ነው በማለት የሚናገሩ ሰዎችን መስማት አዋጭ አይደለም፡፡ ይህ ከጥቃቱ በኋላ አንዳንድ ሙስሊሞች በኦፕራ ላይ የተናገሩት ነበር፡፡

የተለያዩ የምልክት ድምፆችን ስንሰማ ግራ ይገባናል፡፡ ፕሬዚዳንታችን እና ሌሎች የመንግሥት መሪዎች “እስልምና የሰላም ኃይማኖት ነው” የሚሉትን የሚመስሉ ንግግሮችን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ሌሎች መሪዎች እስልምና የሰላም ኃይማኖት አይደለም በማለት ሲናገሩ ደግሞ እንሰማለን፡፡ ክርክሩም እንደቀጠለ ነው፡ እውነተኛው እስልምና ምንድነው? በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ሙስሊም መሪዎች የሚናገሩት ነውን? ወይንስ በአፍጋኒስታን ወይንም ደግሞ በፓኪስታን የሚገኙ ሙስሊም መሪዎች የሚናገሩት ነው?

በተከታዮቹ ምዕራፎች ውስጥ ነቢዩ መሐመድ የመጀመርያውን የቁርአን ጥቅስ በ610 ዓ.ም. አካባቢ ከተቀበለበት ጊዜ አንስቶ የእስልምና አስኳል ስለሆነው የሽብርተኝነት ስረ መሰረት ጠቃሚ የሆነ ትንታኔን ታነባላችሁ፡፡ ይህ ስር ከመሐመድ በመነሳት እስከዚህ ዘመን ድረስ ተያይዞ ይመጣል፡፡

ይህንን መጽሐፍ ለየት የሚያደርገው በዓለም ላይ አለ በሚባል የእስልምና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የእስልምና ታሪክ ፕሮፌሰር በነበረ ሰው የተፃፈ መሆኑ ነው፡፡ ስለ እስልምና እና ስለ ሽብርተኝነት የሚያወሩት በአካባቢያችሁ ከሚገኙ የመጻሕፍት መደብሮች የምትገዟቸው መጻሕፍት በአሜሪካውያን ጋዜጠኞች፣ በአሜሪካውያን  ፖለቲከኞች፣ የቀድሞ የሲ.አይ.ኤ. ሰራተኞች ወዘተ. በሆኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡ ዶ/ር ገብርኤል ከእነርሱ የማትሰሟቸውን የዕይታ ነጥብ ያቀርባል - እስልምናን የኖረ፣ እስልምናን ያጠና፣ እስልምናን ያስተማረ እና እስልምናን በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ መስጊዶች ውስጥ የሰበከ ሰው የዕይታ ነጥብ፡፡ ይህ በእስልምና ጥናት የማስተርስ ዲግሪውንና ዶክትሬቱን ያገኘ ሰው ነው፡፡ ይህ ሕይወቱን ከአንድ ጊዜ በላይ በሙስሊም አክራሪዎች እጅ ሊያጣ የተቃረበ ሰው ዕይታ ነው፡፡ ሰውነቱ ያንን ጠባሳ የሚያሳይ ሲሆን ታሪኩንም በመጽሐፉ ጅማሬ ላይ ይተርካል፡፡

ዶ/ር ገብርኤል ምዕራባውያን ሰምተውት የማያውቁትን የመሐመድን ታሪክ እውነታ ይገልጣል፡፡ በእርግጥም ሙስሊም አክራሪዎች እስልምናን የሚለማመዱት ልክ መሐመድ ሲለማመድ እንደነበረው መሆኑንም ያሳያል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ከኖረ ሰው የዕይታ ነጥብ ባለፉት  ጥቂት አስርተ ዓመታት የታየውን የሽብርተኛነት ዕድገት ያብራራል፡፡ ቁልፍ የሆኑ ፋላስፎችን በመለየት አደገኛ ከመሆናቸው የተነሳ በመካከለኛው ምስራቅ መንግሥታት የታገዱትን እና ደራሲያኖቻቸው ደግሞ የተገደሉትን መጻሕፍት ይዘቶች ይነግራችኋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት የሚገኙት በጥቁር ገበያ ላይ ብቻ ነው ነገር ግን የሽብርተኝነትን እሳት እያቀጣጠሉ ያሉ ነዳጆች ናቸው፡፡

ፅንፈኛ ከሆኑ እርምጃዎች በስተጀርባ ያሉትን ኃይማኖታዊ መሰረቶች ያብራራል፡፡ አንድ ሰው በአላህ ስም ጄት በመከስከስ ስለምን ራሱን ያጠፋል? መልሱ የሚገኘው በሥራ የተሞላ ነገር ግን ተስፋ የለሽ በሆነ የእምነት ሥርኣት ውስጥ ነው፡፡

አንዳንድ እውነታዎች የሚረብሹ ናቸው - ይህ በዓለም ውስጥ ተመቻችቶ ያለ ትልቅ አቅም ያለው ክፋት ነው - ነገር ግን አጠቃላይ የዚህ መጽሐፍ መልዕክት የሰላምን ስሜት ይፈጥራል፡፡ በዜናዎች የምንሰማቸው የተነጣጠሉ ክስተቶች በሙሉ በእስላማዊ ፅንፈኝነት መዋቅር ውስጥ ስንመለከታቸው ትርጉም ይሰጡናል፡፡ ከስጋዊው ውጊያ በስተጀርባ ያለው መንፈሳዊው ውጊያ አሁን ግልፅ ይሆናል፡፡

ዶ/ር ገብርኤል እንዲህ በማለት ያሳስቡናል፡ “ከሽብርተኝነት በስተጀርባ ያለው እስልምና እንጂ ሙስሊሞች አይደሉም፡፡ ሙስሊሞች ተጠቂዎች ናቸው፡፡ አውሮፕላኖችን በመጥለፍ በመከስከስ የሞቱት አስራ ዘጠኙ ወጣቶች እንኳ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ወንጀለኛው እስልምና ነው፡፡”

ዶ/ር ገብርኤል ስለ ወደፊቱ የተስፋ ራዕይ አላቸው፡፡ እስልምና ዓለምን የመቆጣጠር አጀንዳ እንዳለው ሁሉ በእስልምና ወጥመድ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ እግዚአብሔርም ብዙዎችን የማዳን አጀንዳ አለው፡፡

   
ጄ. ሊ ግሬዲ
የካሪዝማ መጽሔት አርታኢ

 

ወደ ማውጫው መመለሻ

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ