የቁርአን ውስጥ ቅራኔዎች

ከአዘጋጁ

 

ቁርአን በሰማይ ከተጠበቀው የመጽሐፍ ማህደር ውስጥ ተጠብቆ ያለና ከዚያ ላይ የመጣ መጽሐፍ እንደሆነ ስለራሱ ይናገራል 85.21-22፡፡ ከአላህ የመጣ ፍፁም መጽሐፍ ከሆነ ቁርአን በውስጡ እርስ በእርሱ የሚቃረን ምንም ነገር ሊኖረው አይገባም፡፡ ወይም ደግሞ የሚቃረኑ ለሚመስሉ ነገሮች ሎጂካዊ መልስ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ ሙስሊሞች በሙሉ ቁርአን ምንም ቅራኔ የለበትም በማለት እንደሚናገሩ እናውቃለን ይሁን እንጂ በቁርአን ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ እርስ በእርስ የሚቃረኑ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም በዚህ ጽሑፍ መዳሰስ የማይቻል ቢሆንም፤ ከዚህ በመቀጠል በጣም ጥቂት የሆኑትን ቅራኔዎች ሙስሊሞች እንዲያስተውሏቸው አስፍረናል፡፡

እዚህ ያሰፍርናቸው አንዳንዶቹ ቅራኔዎች አከራካሪዎች ይመስላሉ ነገር ግን በትክክል የተወሰዱት ከራሱ ከቁርአን ውስጥ ነው፡፡ እነሱም ምንም ማመካኛና ማስተባበያ የማይሰጥባቸው ቅራኔዎች ናቸው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ቅራኔ የሚለውን ነገር መተርጎም ለአንባቢ የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡ አንድ ሐሳብ ከሌላ ሐሳብ ወይንም አባባል ጋር ይቃረናል የምንለው - የአንድ አረፍተ ነገር ሐሳብ የሌላውን ዓረፍተ ነገር ሐሳብ ወይንም መኖር መቻል ሙሉ ለሙሉ ሲሽር ወይንም የቀደመው ሐሳብን እንዳልኖረ አድርጎ አዲስን ሐሳብ ሲያስቀምጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ቁርአን 9.67 የሚናገረው ሰው ከምንም እንደተፈጠ ሲሆን 15.26 ላይ ደግሞ ሰው ከሸክላ እንደተፈጠረ ይናገራል፡፡ ሸክላ አንድ ነገር ስለሆነ ሰው ከምንም ተፈጠረ ከሚለው ጋር ቅራኔ አለው ማለት ነው፡፡ ማለትም ምንም ነገር የሚለው ሸክላ የሚለውን የሚሽር ወይንም የማይጨምር ነውና፡፡ ስለዚህም በዚህ ነጥብ ላይ ብቻ እንኳን በሰው አፈጣጠር ሐሳብ ላይ ሁለቱ ሐሳቦች በማንኛውም መንገድ ቢታዩ ትክክል ሊሆኑ አይችሉምና ነው፡፡

ስለዚህም ከዚህ በታች ያሉትን የእርስ በእርስ መቃረን ጥቅሶች እንደናሙና እናቀርባለን ጥቅሶቹም ሙሉ በሙሉ የተወሰዱት 1997 በነጃሺ አሳታሚ ከታተመው ቁርአን ውስጥ ነው፡፡

1. በቁርአን መሠረት በሃይማኖት ማስገደድ አለ ወይንስ የለም?

. በሃይማኖት ማስገደድ የለም ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው 2.256፡፡

. (ይህ) ከአላህና ከመልክተኛው በታላቁ ሐጂ ቀን የወጣ አላህ ከአጋሪዎቹ ንጹሕ ነው መልክተኛውም (እንደዚሁ) (ከክህደት) ብትጸጸቱም እርሱ ለናንተ በላጭ ነው (ከእምነት) ብትሸሹም እናንተ አላህን የማታቅቱት መሆናችሁን ዕወቁ በማለት ወደ ሰዎች የሚደርስ ማስታወቂያ ነው እነዚያን የካዱትንም በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው 9.3፡፡

. የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው ያዙዋቸውም ክበቡዋቸውም ለነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ ቢጸጸቱም ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና 9.5፡፡

. ከነዚያ መጽሐፍትን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው 9.29፡፡

ከዚህም በላይ ባየናቸው አራት ጥቅሶች ውስጥ ከሙስሊም የተለየ ሃይማኖትን ስለመከተል ቁርአን የሚናገረው ሁለት ዓይነት ነገርን ነው፡፡ ሁለቱም ደግሞ እርስ በእርስ የተቃረኑና በምንም ሊታረቁ የማይቻሉ ናቸው፡፡ በሃይማኖት ማስገደድ የለም ደግሞ ቆይቶ በሃይማኖት ማስገደድ እንዲያውም የማይቀበለውን መቅጣት ብሎም መግደል ካልሆንም ግብር ማስከፈልን ይናገራል፡፡ ታዲያ ይህ እልም ያለ ተቃርኖ አይደለምን? ነው እንጂ! ስለዚህም ቁርአን ከእግዚአብሔር ሊሆን እንዴት ይችላል?

2. የመጀመሪያው ሙስሊም ማን ነበር? መሐመድ ነበርን? አብርሃም ነበርን? ያዕቆብ ነበርን? ወይንስ ሙሴ ነበርን? በእርግጥ የመጀመሪያው ሙስሊም ማን ነበር? ቁርአን ስለመጀመሪያው ሙስሊም የሚከተለውን ነገር ይናገራል፡፡

. የሙስሊሞችም መጀመሪያ እንደሆን ታዘዝኩ (ማለትም መሐመድ) 39.12፡፡

. ሙሳም ለቀጠሯችን በመጣና ጌታውም ባነጋገረው ጊዜ - ጌታዬ ሆይ! (ነፍስህን) አሳየኝ ወደ አንተ እመለከታለሁና አለ (አላህም) - በፍፁም አታየኝም ግን ወደ ታራራው ተመልከት በስፍራውም ቢረጋ በእርግጥ ታየኛለህ አለው ጌታውም ለተራራው በተገለጸ ጊዜ ንኩትኩት አደረገው ሙሳም ጮሆ ወደቀ በአንሰራራም ጊዜ ጥራት ይገባህ ወዳንተ ተመለስኩ እኔም (በወቅቱ) የምዕመናን መጀመሪያ ነኝ አለ፡፡ 7.143፡፡

. በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ ያዕቁብንም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ) ልጆቼ ሆይ አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ (አላቸው) 2.132፡፡

እንግዲህ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች መሠረት የመጀመሪያው ሙስሊም ማን እንደሆነ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ ይህም ቁርአን ስለዚህ ትልቅ ነገር እንኳን የጠራ ነገር እንደሌለው የሚያስረዳ እውነታ ነው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ የምንሰማውና - ሰው ሁሉ እስላም ሆኖ ተወልዷል - የሚለው የሙስሊሞች አነጋገርንም አይደግፈው፡፡ ሰው ሁሉ ሙስሊም ሆኖ ነው የተወለደው የሚለውን ሐሳብ ሙስሊሞች ከየት አመጡት ከቁርአን ላይ ወይስ ከየት? ከዚህ በላይ ያሉት ጥቅሶች እርስ በእርስ መቃረናቸው ብቻ ሳይሆን ይህንንም ሰው ሁሉ የተወለደው እስላም ሆኖ ነው የሚለውን አባባልና አመለካከት ጭምር መሠረት የሌለው ያደርጉታል ለዚህም ማስረጃችን እራሱ ቁርአን ነው፡፡  

3. የሐሰት አማልክት የሚያመልኩትን አላህ ይቅር ይላል ወይንስ አይልም?

. አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኃጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኃጢአት በእርግጥ ቀጠፈ 4.48 እንዲሁም ደግሞ አላህ በእርሱ የማጋራትን (ወንጀል) አይምርም ከዚህም ወዲያ ያለውን ለሚሻውም ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው (ከውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ 4.116፡፡

. የመጽሐፉ ሰዎች በነሱ ላይ ከሰማይ መጽሐፍን እንድታወርድ ይጠይቁሃል ከዚያም የከበደን ሙሳን በእርግጥ ጠይቀዋል አላህንም በግልፅ አሳየን ብለዋል በበደላቸውም መብረቅ ያዘቻቸው፡፡ ከዚያም ታምራቶች ከመጡዋቸው በኋላ ወይፈኑን (አምላክ አድርገው) ያዙ ከዚያም ይቅር አልን፡፡ ሙሳንም ግልጽ ስልጣንን ሰጠነው 4.153፡፡

ከዚህ በላይ ያሉት ጥቅሶች ግልጥ እንደሚያደርጉት ሁሉ ሌላ አማልክት የሚያመልኩ ይቅር አይባሉም ይሉና እንደገና ደግሞ፤ ወይፈን (ጣዖት) ያመለኩትን ይቅር አልናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህ የቁርአን ጥቅሶች የሚገርሙ ናቸው የሚያሳዩትም በሙስሊሞች አላህ ባህርይና በሙስሊሞች የይቅርታ አስተምህሮ ላይ ግልጥ የሆነ ቅራኔ እንዳለ ነው፡፡

4. የአላህ ትዕዛዛት ሊቀየራሉ ይችላሉ ወይንስ ሊቀየሩ አይችሉም?

. ከበፊትም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፤ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሡ የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም ከመልክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ፡፡ 6.34፡፡

. የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትሆን ተፈፀመች ለቃላቱ ለዋጭ የለም እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡ 6.115፡፡

. ከአንቀፅ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይንም ብጤዋን እናመጣለን አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መኾኑን አታውቅምን? 2.106፡፡

. በአንቀፅም ስፍራ አንቀፅን በለወጥን ጊዜ አላህም የሚያወርደውን ነገር ዐዋቂ ነው አንተ ቀጣፊ እንጂ ሌላ አይደለህም ይላሉ በውነቱ አብዛኞቻቸው አያውቁም 16.101፡፡

እነዚህ አራት ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ከሆነ - የአላህ ትዕዛዛት አንድ ጊዜ ይቀየራሉ ሲሉ ቀጥሎ ደግሞ አይቀየሩም በማለት ነው፡፡ ታዲያ የትኛውን ነው ለእምነት መመሪያ አድርገን መያዝ የሚገባን ይቀየራሉ የሚለውን ነው ወይንስ አይቀየሩም የሚለውን? ነገሩ ከባድ ነው የቁርአንን ታማኝነት ብቻ ሳይሆን እንድንጠይቅ የሚያደርጉን የሙስሊሞችንም አምላክ ባህርይ ነው፡፡

5. የሰውንስ ተፈጥሮ በተመለከተ ቁርአን ወጥ ትምህርት አለውን? ለመሆኑ  በቁርአን መሰረት ሰው ከምንድነው የተፈጠረው ከደም ነውን? ከሸክላ ነውን? ከአፈር ነውን? ከሚገማ ጥቁር ጭቃ ነውን? ወይንስ ከምንም ነገር ነውን?

. ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም) 96.2፡፡

. ሰውንም ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጥቁር ጭቃ በእርግጥ ፈጠርነው 15.26፡፡

. አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው ከዐፈር ፈጠረው ከዚያም ለርሱ (ሰው) ኹን አለው ኾነም 3.59፡፡

. ሰው ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን እኛ የፈጠርነው መኾኑን አያስታውስምን? 19.67፡፡

. ሰውንም ከፍትወት ጠብታ ፈጠረው ከዚያም እርሱ ወዲያውኑ (ትንሳኤን በመካድ) ግልፅ ተከራካሪ ይሆናል 16.4፡፡

ከዚህ በላይ በግልፅ ከተቀመጡት የቁርአን ጥቅሶች ውስጥ በትክክል ሰው ከአምስት የተለያዩ ነገሮች እንደተፈጠረ ነው፡፡ የትኛው ነው ትክክል? ስለ ሰው አፈጣጠር ሙስሊሞች ከእነዚህስ ውስጥ ስለየትኛው ነው በትክክል መናገር የሚችሉት? ይህስ የተለያየ የሰው አፈጣጠር ዋና ቅራኔ አይደለምን? ነው እንጂ!

6. ወይን (የሚያሰክር አልክሆል) መጠጣት ጥሩ ነገር ነው ወይንስ መጥፎ?

. እናንተ ያመናችሁ ሆይ የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጣዖታትም አዝላምም ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው (እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጅላልና 5.90፡፡

. የዚያች ጥንቁቆቹ ተስፋ የተሰጧት ገነት ምስል በውስጧ ሺታው ከማይለውጥ ውሃ ወንዞች ጣዕሙ ከማይለውጥ ወተትም ወንዞች ለጠጪዎች ሁሉ ጣፋጭ ከኾነች የወይን ጠጅም ወንዞች ከተነጠረ ማርም ወንዞች አሉባት ለነሱም በውስጧ ከፍሬዎች ሁሉ (በያይነቱ) ከጌታቸው ምሕረትም አላቸው (በዚች ገነት ውስጥ ዘውታሪ የኾነ ሰው) እርሱ በእሳት ውስጥ ዘውታሪ እንደ ኾነ ሰው ሞቃትንም ውሃ እንደ ተጋቱ አንጀቶቻቸውንም ወዲያውኑ እንደ ቆራረጠው ነውን? አይደለም፡፡ 47.15፡፡

. እውነተኞቹ ምእመናን በእርግጥ በድሎት (ገነት) ውስጥ ናቸው፡፡ በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ኾነው ይመለከታሉ፡፡ በፊቶቻቸውም ላይ የድሎትን ውበት ታውቃለህ፡፡ ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጥጠጣሉ 83.22-25፡፡

ከዚህም በላይ ስለ አልክሆል መጠጣት የቀረበው ግልጥ የሆነ ተቃርኖ ነው፡፡ አማኞች እዚህ ምድር ውስጥ አልኮሆል መጠጣት ተከልክለዋል ነገር ግን በገነት ውስጥ ይፈቀድላቸዋል፡፡ በቅዱስ ቦታ በገነት ውስጥ መጠጣት የሚፈቀድ ከሆነስ ገነት፣ ገነት ሊሆን ይችላልን?

7. ፈርዖን በውሃ ውስጥ ሰጥሞ ሞቷል ወይንስ አልሞተም?

. የእስራኤልም ልጆች ባሕሩን አሳለፍናቸው ፈርዖንና ሰራዊቱም ወሰን ለማለፍና ለመበደል ተከተሏቸው መስጠምም ባገኘው ጊዜ - አመንኩ እነሆ ከዚያ የእስራኤል ልጆች በርሱ ከአመኑበት በስተቀር ሌላ አምላክ የለም እኔም ከታዛዦቹ ንኝ አለ፡፡ ከአሁን በፊት በእርግጥ ያመጥክ ከአጥፊዎች የነበርክ ስትኾን አሁን (አመንኩ ትላለህ)? ዛሬማ ከኋላህ ላሉት ታምር ትኾን ዘንድ በድን ኾነህ (ከባሕሩ) እናወጣሃለን (ተባለ) ከሰዎችም ብዙዎቹ ከታምራታችን በእርግጥ ዘንጊዎች ናቸው 10.90-92፡፡

. (ሙሳም) - እነዚህን (ታምራቶች) መገሰጫዎች ሲኾኑ የሰማያትና የምድር ጌታ እንጂ ሌላ እንዳላወረዳቸው በእርግጥ ዐውቀሃል እኔም ፈርዖን ሆይ የምትጠፋ መኾንህን በእርግጥ እጠረጥርሃለሁ አለው፡፡ ከምድርም ሊቀሰቅሳቸው አሰበ እርሱንና ከርሱ ጋር የነበሩትንም ሰዎች ሁሉንም አሰጠምናቸው 17.102-103፡፡

የፈርዖንምፍፃሜ ታሪክ ቁርአን የሚያቀርበው ሁለት ዓይነት አድርጎ ነው፡፡ በአንድ ቦታ ሰጥሟል በሌላው ላይ ይህ እንዳልተነገረ ተቆጥሮ አልሰጠመም ተባለ ስለዚህም እርስ በእርስ የሚቃረን አይደለምን?

እነዚህ ቁርአን ውስጥ ያሉ የባለ ሰባት ነጥብ የእርስ በእርስ ቅራኔዎች በግልጥ የሚያሳዩት በቁርአን ውስጥ ለማስረዳት የሚያስቸግሩ ቅራኔዎች መኖራቸውን ነው፡፡ እነዚህ የቀረቡት ለምሳሌ ብቻ ሲሆን ሌሎች እጅግ በርካታ ቅራኔዎች ይገኛሉ፡፡ ቅራኔዎች ምን ያመለክታሉ? በአንድ ሐሳብ ላይ እርስ በእርስ የሚቃረን ነገር በአንድ ሰነድ ውስጥ ከተገኘ የሰነዱ ጸሐፊ ወይንም ምንጭ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ በቁርአን ላይ ያሉት እጅግ ብዙ ቅራኔዎች በትክክል የሚጠቁሙት ቁርአን ከእግዚአብሔር የመጣ መልእክት አለመሆኑን ነው፡፡

ይህ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የምንከተለውን እምነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል የመጨረሻችንም ተስፋ ቢስ ፍፃሜ የሚሆን ለመሆኑ ይጠቁመናል፡፡ ታዲያ ምንድነው ማድረግ የሚኖርብን? ይህ በትክክል አሳሳቢ ጉዳይ ነው፣ ጉዳዩም የዘላለምን ሕይወት የት እንደምናሳልፈው ሁሉ የሚወስን ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊሞች ሁሉ እንድታስቡበትና ወደ እውነተኛውና ምንም ቅራኔ ወደሌለበት ወጥ የሆነ ትምህርት ወዳለውና በቀጥታ ከእግዚአብሔር ወደ መጣው መጽሐፍ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንድትመጡና መልእክቱን ለራሳችሁ እንድታነቡ እንጠይቃችኋለን፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊ መልእክት ሰው ኃጢአተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከእግዚአብሔር የራቀ መሆኑን እና ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ የሚችለው ስለ ኃጢአት በተሰጠው የመስዋዕትነት ሞት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ መስዋዕቱን እግዚአብሔር እራሱ አዘጋጅቶ አዳኙን ጌታ ኢየሱስን በኃጢአተኞች ምትክ በመሞት ዋጋ እንዲከፍል አደረገው፡፡ ኃጢአቱንም በእውነት ተናዞ በእሱም በአዳኙ የሚታመን ማንም ቢኖር የኃጢአቱን ይቅርታና የዘላለምን ሕይወት እንደሚቀበል ነው፡፡ ነገሩ እውነት ነው እኛም የኃጢአትን ይቅርታ አግኝተን በእሱ በኩል የዘላለምን ሕይወት ስጦታ ተቀብለናል፡፡ እናንተም ብትመጡ ይህንን ለራሳችሁ ታያላችሁ በሕይወታችሁም ውስጥ ታላቅ ለውጥን ታያላችሁ ኑ ወደ ጌታ ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት ታገኛላችሁ፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ