እስላማዊ ሕግ

M. J. Fisher, M.Div

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

በዚህ የአንድ መቶ ስድስት ጥቅሶች ስብስብ ውስጥ እንደሚታየው ቁርአን በሰፊው የሚያተኩረው እስላማዊ ሕጎች ላይ ነው፡፡ እስልምና እጅግ በጣም ሕጋዊ የሆነ ሃይማኖት ነው፡፡ መልእክቱንም ማዕከላዊ በማድረግ የመሠረተው በሕግ ላይ ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ ላሉት ትእዛዛት እንዲሁም በሙስሊም ትውፊታዊ ታሪካዊ መጽሐፍ ‹ሃዲት› ውስጥ ላሉት ሙሉ ለሙሉ በመሰጠት መታዘዝን አጥብቆ ይናገራል፡፡ በቁርአን ውስጥ ያሉት ሕጎች ብዙዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልካም ነገርና ከአረባዊ  ጥሩ ሐሳቦች እንዲሁም ከቀደምት የጣዖት አምልኮ ስርዓቶች የተውጣጡ ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሴቶች ማለትም እንደ እምነት፣ መታዘዝ፣ ፀሎት፣ ደግነት፣ ፅድቅ እና ጋብቻ በቁርአን ውስጥ ለማስረጃነት መቅረባቸው ግልጥ ነው፡፡ ሙስሊሞች ቁርአን የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ቀጣይ ትምህርት ነው በማለት ስለሚያምኑ ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ አንዳንዶቹ እሴቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ጋር ይቀራረባሉ አንዳንዶቹ ደግሞ በመሐመድ ጊዜ የነበረውን አረባዊ ባህልን ያንፀባርቃሉ፡፡ ጋብቻም ይህንን እውነታ ለማሳየት ከሚጠቅሙት ውስጥ አንዱ ነገር ነው፡፡ ቁርአን ብዙ ጋብቻን (ፖሊጋሚን)፣ በጦርነት የተማረኩትን ባሪያዎችን ቅምጥ ማድረግን ሁሉ ይፈቅዳል፡፡ አንድ ሰው የእንጀራ ልጆቹን እና እናታቸውንም ማግባት ይችላል፡፡ አንድ ሰው የልጁን ሚስት ማግባት ይችላል ይህም የጉዲፈቻ ልጁ ሚስቱን ከፈታት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሕጎች ለክርስትያኖች ባዕዶች ናቸው፡፡

እስልምናም ክርስትናም የፅድቅ ሕይወት ጠቃሚነት ላይ ትኩረትን ይሰጣሉ ነገር ግን ‹ወርቃማው ሕግ› በቁርአን ውስጥ የሌለ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ዋና ነገር ነው፡፡ ይህም ሕግ፡- ‹እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።› ማቴዎስ 7.12፡፡ ከዚህ ጋር የሚስማማ ትምህርት በመሐመድ ቁርአን ውስጥ አልተወሳም አይገኝምም፡፡

ሌላው ለመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ልዩ የሆነው ትምህርት ‹ፀጋ› ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፀጋ አዲስ ኪዳን የሚተረጉመው እኛ በምንም መንገድ ልናገኘው የማይገባን ሙሉ ምህረት እና እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር እንደሆነ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ፍቅር ማወቅ ክርስትያኖችን ከጭንቀትና የማይችሉትን ነገር እንዳይሞክሩ ያደርጋቸዋል ይህም የማይቻለው ነገር በመልካም ስራቸው የእግዚአብሔርን ፅድቅ ለማግኘት መሞከር ነው፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ፀጋ ከእግዚአብሔር ምህረትን በስራ ለመቀበል እንዳይሞክሩ (አይቻልምና) ያደርጋቸዋል ከዚያም በፀጋውና በነፃ ስጦታው እግዚአብሔርን እንዲያስደስቱ የሚያስችላቸውን ብቁ ኃይል ይሰጣቸዋል፡፡ እነሱም ከአሁን በኋላ በሕግ በኩል ፅድቅን ለማግኘት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመሞላት በመንፈስ ይኖራሉ ሮሜ 8.1-4፡፡

ፀጋ በክርስትያኖች ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደሚሰራ አንዱ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው ከቀላል የትራፊክ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ በሕግ የሚኖረው ሰው በትምህርት ቤት ክልል አካባቢ ገብቶ የመኪና ፍጥነት ሜትሩን ይመለከታል ይህም ሕጉን ማክበሩን እርግጠኛ ለመሆን ነው፡፡ በመንፈስ የሚኖረው ሰው ግን በትምህርት ቤት አካባቢ ሲገባ ዝግ በማለት መንገድን ለማቋረጥ የሚመጡ ወይንም ደግሞ ኳስ ለመመለስ የሚሮጡ ልጆች መኖር አለመኖራቸውን በአካባቢው ይቃኛል፡፡ እውነተኛ ክርስትያኖች ሪፖርት እንዳደረጉት ሕጉን ለመፈፀም የሚያነሳሳቸው ነገር ከሲዖል ፍርሃት ይልቅ የፀጋው ፍቅር ግንዛቤ እጅግ በጣም ጠንካራ እንደሆነ ነው፡፡

ይህ አስደናቂ ፀጋ በክርስትያኖች የእምነት ስርዓት ውስጥ ማለትም እንደ ጥምቀት እና የጌታ እራት ውስጥ ይንፀባረቃል፡፡ እነዚህ ስርዓቶች በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች ከተሰጡት እንደ ግርዛትና የፋሲካ በዓል እራት አበላል የቀጠሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ የአይሁድ ስርዓቶች አከባበርና ትርጉም በመሲሁ በሚያምኑት ተቀይረዋል ይህም የሆነው በመስቀሉና በትንሳኤው አማካኝነት ነው፡፡

በተመሳሳይ መንገድ በእስልምና ሕግ የታዘዙት ስርዓቶች ከመሐመድ በፊት በመካ ይኖሩ በነበሩት የጣኦት አምላኪዎች ይከበሩ ከነበሩት ስርዓቶች የቀጠሉ ናቸው፡፡ እነሱም እራሳቸው በእስልምና አንድ አምላክ አምልኮ ዓይነት ስርዓት ውስጥ ተካተዋል፡፡ በእርግጥም በመሐመድ ዘመን የነበሩት ፓጋኖች ወይንም የጣዖት አምላኪዎች በቁርአን ውስጥ የተጠቀሱትን ብዙዎችን ልምምዶች ይለማመዷቸው ነበር፡፡ ከእነዚህም ልምምዶች ውስጥ ለምሳሌ ወደ መካ ጉዞን ማድረግ፣ በሰፊ ቦታ ላይ የነበረውን ካዓባ የተባለውን አራት ማዕዘናዊ ግንብ ከብቦ መዞር፡፡ በመካ አቅራቢያ የሚገኘውን የተቀደሰ ጉብታ ወይንም ተራራ መጎብኘት እንዲሁም ደግሞ የአንድ ወር ፆም ይገኙባቸዋል፡፡ ለመሐመድ የፓጋን ጎሳ የነበረው በጣም ታዋቂው የጣዖት ስም ‹አላህ› የሚለው ስም ነበር፡፡ የሐሺም ጎሳ የሆነውና የመሐመድ ቅርብ ዘመድ ጎሳ በመካ የሚገኘው የካዓባ ጠባቂ ነበር፡፡ ግንቡም 45 ጫማ ከፍታ እና 33 ጫማ ስፋት እንዲሁም 50 ጫማ ርዝመት ያለው ነው፡፡ መሐመድ ብዙ ነገሮችን ጠይቋል፡፡ እሱም ያለው አላህ ብቻ ነው ብቸኛ አምላክ፣ አላህ ከሰዎች ሁሉ አምልኮንና አገልግሎትን ይፈልጋል፣ ይህም በሁሉም ቦታ ከሁሉም ሰው ሲሆን የፓጋን ስርዓቶቹ ግን እንደነበሩ ይቀጥላሉ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በካዓባ ውስጥ ያሉት ሌሎቹ ጣዖታት ከተወገዱ በኋላ ነው የሚል ነበር፡፡ በካዓባ ውስጥ እንዲቀር የተፈቀደለት አንድ ነገር ጥቁሩ ድንጋይ ብቻ ነበር፡፡ ልክ ፓጋኖቹ ከመሐመድ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ይህ ድንጋይ ምናልባትም ተወርዋሪ ኮከብ በሙስሊሞች ተከብሮ ይሳማል እንዲሁም በእሱ ዙሪያ ሙስሊሞች ሁሉ ይዞራሉ፡፡ እነዚህንም ነገሮች ማሟላት ማለት ለእልምና ማዕከላዊ ነገር ነው ምክንያቱም ሙስሊሞች የሚያምኑት እነዚህ የተመሰረቱት በአብርሃም ነው በማለት ነውና፡፡

ስለዚህም ቁርአን የሚከተሉትን ይናገራል፡

የእምነት አንቀፅ፡- ሙስሊሞች ሁሉ ‹እርሱ አላህ አንድ ነው፣ አላህ የሁሉ መጠጊያ ነው አልወለደም አልተወለደምም ለርሱም አንድም ብጤ የለውም› 112.1-4 ማለት አለባቸው፡፡

ሌሎች አማልክትን አትቀበሉ፡- ‹... ከአጋሪዎችም አትሁኑ› 30.31፡፡

ወደ መካ ስገዱ፡- ከሰዎቹ ቂሎቹ ከዚያች መሐመድ በመጀመሪያ ወደ እየሩሳሌም ስገዱ በማለት ካዘዘው ትዕዛዝ ወደ መካ በመቀየሩ ለምን እንደሆነ ይጠይቃሉ 2.142፡፡ በምትፀልዩበት ጊዜ ፊታችሁን ወደ ተከበረው መስጊድ ወደ ካዓባ አዙሩ 2.142፡፡

የቀደሙት የፓጋን ስርዓቶች ቀጥለዋል፡- ሁለቱ ጉብታዎች ሳዓፋ እና ማርዋ ለአላህ ምልክቶች ናቸው ስለዚህም ወደ መካ ለሚጓዝ ተጓዥ ወይንም ለጎብኝ በእነሱ ዙሪያ መጓዝ ምንም ኃጢአት አይደለም (ልክ ፓጋኖቹ የአምልኳቸው አንድ ክፍል አድርገውት እንደነበረው ሁሉ ማለት ነው) 2.158፡፡

መካን መጎብኘት ስራ፡- ለሰዎች ልጆች ሁሉ የተገነባውና የተወሰነው የመጀመሪያው ቤተመቅደስ በመካ ነበር፡፡ አብርሃም የቆመበትና የፀለየበት ቦታ እዚያ ነበር፡፡ ስለዚህም ጉዞውን ለማድረግ ለሚችሉ ሙስሊሞች ሁሉ ወደ መካ መጓዝ ግዴታ ነው 3.96፣ 97፡፡

የፓጋን ስርዓቶች ተቀይረዋል፡- ከመካ ጉዞ በመመለስ ጊዜ (ፓጋኖቹ ሁልጊዜ ወደ ቤታቸው የሚገቡት ከጓሮ በኩል ነበር) ሙስሊሞች ግን ወደ ቤታቸው በፊት ለፊት በር በኩል ለመመለስ ይችላሉ፡፡ ለፃድቃን በየትኛው በር በኩል ወደ ቤት የመመለሳቸው ጉዳይ ምንም ችግር የለበትም፡፡ አላህን ፍሩ ደግሞም በተገቢው በር በኩል ግቡ 2.189፡፡

ፆም፡- በረመዳን ወር ሙስሊሞች ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ መፆም አለባቸው፡፡ የማይችሉ ከሆነ ድሃዎችን በመመገብ እራሳቸውን ነፃ ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የጨረቃ ወቅት መለዋወጥ የተደረገው የሰው ልጆች ወደ ጉዞ መቼ ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ነው 2.183-189፡፡

አርብ፡- በአርብ ቀን ለማምለክ ተጣደፉ፡፡ ስራችሁንም ከመስራት አቁሙ፡፡ ይህ ነው ሕጉ ነገር ግን የመሐመድ ተከታዮች አብዛኛዎቹ በአርብ ቀን ንግድ ወይንም የሸቀት ዋጋ ድርድር ወይንም የሆነ አስደናቂ ነገርን ባዩ ጊዜ (መጣደፉን ወይንም ወደ አምልኮ መሄዱን) ትተውታል 62.9-11፡፡

ውጊያ፡- አላህ ለእስልምና የሚዋጉትን ይመራቸዋል 29.69፡፡ ሙስሊሞች ሁሉንም መዋጋት አለባቸው እስልምናን የማይቀበሉትን ክርስትያኖችንም አይሁዶችንም ጭምር፣ ይህም እነሱ መደበኛ የሆነ የገንዘብ ክፍያ በማድረግ እራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ለእስልምና ተዋጊዎች በፈቃዳቸው እስከሰጡ ድረስ ነው 9.29፡፡ ምንም እንኳን መዋጋትን ባይወዱትም ለሙስሊሞች ሁሉ መዋጋት ግዴታ ነው 2.216፡፡

የጦር ምርኮ አንድ አምስተኛው፡- ከጣዖት አምላኪዎች ጋር ተዋጉ ይህም እስልምና ዋናው ሃይማኖት ሆኖ እስከሚገዛ ድረስ ነው፡፡ ለመሐመድ፣ ለመሐመድ ዘመዶች እና ለሚያስፈልጋቸው፣ ለወላጅ አልባዎች እና ለመንገደኞች የምርኮአችሁን አንድ አምስተኛ ስጡ 8.41፡፡

ግድያ፡- ሙስሊሞች አላህ ቅዱሳን ናቸው ያላቸውን መግደል የለባቸውም ይህም ትክክል እስካልሆነ ድረስ ነው 25.68፡፡ ሙስሊሞች ሌሎች ሙስሊሞችን መግደል የለባቸውም ትክክል ባልሆነ መንገድ እንደዚህ የሚያደርጉት ደግሞ በገሃነም ውስጥ ይቃጠላሉ 4.29፣30፡፡

በቀልን አድረጉ ወይንም ይቅር በሉ፡- ለክፉ ነገር እኩል የሆነን በቀል አድርጉ፡፡ አንድ ሰው ይቅርታ ማድረግን ከመረጠ ደግሞ ያ የተሻለ ነው፣ ነገር ግን እራሳቸውን የሚከላከሉ ስህተት የለባቸውም 42.40-41፡፡ ክፉና መልካም የተለያዩ ናቸው፡፡ ክፉውን ነገር በበጎ ነገር ብትቃወም ጠላትህ በጣም ውድ ጓደኛህ ይሆናል 41.34፡፡ ገርን ጠባይ ያዝ፣ በመልካምም እዘዝ ባለጌዎችንም ተዋቸው 7.199፡፡

ለነፍስ ግድያ የበቀል ምላሽ፡- አንድ ሰው ከተገደለ እኩል እስከ ሆነ ድረስ በቀል መመለስ ተፈቅዷል፡፡ ነፃ ሰው ከተገደለ በምትኩ ነፃ ሰው መገደል አለበት፣ ባሪያም ለባርያ ሴትም ለሴት፡፡ የተጎዳው ወገን ይቅር ካለ ግን የገንዘብ ክፍያ መደረግ አለበት 2.178፡፡

ስረ መሰረቱ፡- ፅኑ ሙስሊሞች ይፀልያሉ፣ ለድሃዎች ይሰጣሉ፣ በፍርድ ቀን ያምናሉ፣ ማንም ሰው ከፍርድ ቅጣት ለማምለጥ እና ለመጠበቅ ዋስትና ስለሌለው የፍርድ ቀንን ይፈራሉ፡፡ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፍላጎታቸውን ሚስቶቻቸው ካልሆኑት እና የጦር ምርኮኞች ባሪያዎች ካልሆኑት በስተቀር ይገታሉ እነዚህ የተፈቀዱላቸው ናቸውና፡፡ ፅኑ የሆኑ ሙስሊሞች ቃል ኪዳኖችን ይጠብቃሉ እንዲሁም ደግሞ የታመነ ምስክርነትን ይሰጣሉ 70.22-35 እና 13.18-24፡፡ ቁርአንን የሚያወሱ፣ ፀሎት ስርዓት ላይ የሚገኙ እና ምፅዋትን የሚሰጡት እነዚያ ይሸለማሉ 35.29፣30፡፡ ሙስሊሞች ስለ አላህ መገለጦችና ተዓምራቶች በሚታወሱበት ጊዜ በአክብሮት ይሰግዳሉ 32.15፡፡ እራሱን ለአላህ ያስገዛ ማንም ቢኖር እንዲሁም መልካምን ነገርን ቢሰራ ሕይወትን በእጆቹ ይዟል 31.22፡፡

ከፀሎት ሰዓት በፊት ታጠቡ፡- ለፀሎት በምትነሱበት ጊዜ እጃችሁን እስከ ክንዳችሁ ድረስ ታጠቡ፣ እግራችሁን ደግሞ እስከ ቁርጭምጭሚታችሁ ድረስ እንዲሁም እራሳችሁን ጥረጉ (አሻሹት)፡፡ ውሃ የማይገኝ ከሆነ ደግሞ ንፁህን አሸዋ በመጠቀም እጃችሁንና ፊታችሁን በእሱ አብሱት 5.6፡፡

የፀሎት ሰዓቶች፡- አላህ በማለዳም በምሽትም፣ ፀሐይ ስትጠልቅና ከሰዓት በእኩለ ቀንም 30.17-18 መከበር ይኖርበታል፡፡ አንድ ሰውም በሚፀልይበት ጊዜ እንዲህ ማለት አለበት ‹ምስጋና ለአላህ ለዚያ ልጅን ላልያዘው ለርሱም በንግስናው ተጋሪ ለሌለው ለርሱም ከውርደት ረዳት ለሌለው ይገባው በልም ማክበርንም አክብረው› 17.111፡፡

ትንሽ እንቅልፍ፡- ፃድቃን ሲሞቱ ገነት አትክልት ቦታ ይሄዳሉ ምክንያቱም ጥሩ ሕይወትን ኖረዋልና፣ ትንሽ እንቅልፍን በመተኛት በማለዳና በምሽት ሲፀልዩ ተገኝተዋልና፡፡ ለለማኞችና እርዳታም ላልለመኑት ሁሉ ሰጥተዋልና 51.15-19፡፡ በምድር በስግደትና በመቆም ሌሊቶችን ሲያሳልፉ ነበር ይህም አላህ ወደ ሲዖል እንዳይሰዳቸው በመፀለይ ነበር 25.64-65፡፡

ለይቅርታ ፀልዩ፡- አላህ ብቻ እንጂ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ስለ ስህተታችሁ ለይቅርታ ለምኑት እንዲሁም ለሌሎችም አማኞች ሁሉ ምክንያቱም እርሱ የትም ብትሄዱ ያውቃልና 47.19፡፡ ይቅር እንዲላችሁ አላህን ጠይቁት ምክንያቱም እርሱ ብዙውን ጊዜ መሐሪ ነውና 73.20፡፡

ጥራት ያላቸው ነገሮች፡- እምነት መልካም ስራዎች ፍትህ እና ቆራጥነቶች እነዚህ የሙስሊም ምልክቶች ናቸው 103.3፡፡ እነሱም በምድር ላይ በትህትና ይመላለሳሉ ዕውቀት ለሌለበትም ንግግር ‹ሰላም› በማለት ይመልሳሉ 25.63፣ 17.37፡፡

ዝሙት፡- ዝሙት ክልክል ነው 25.68፡፡ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚፈቀደው በአንድ ጊዜ ለአራት ሚስቶች ብቻ ነው፡፡ የአዲስ ሚስት ሴት ልጅ ከአራተኛ ሚስቶች እንደ አንዷ ልትወሰድ ትችላለች ይህም ከእናትየው ጋር ያለው ጋብቻ ገና ካልተፈፀመ ነው፡፡ የግብረ ስጋ ግንኙነቶች በጦርነት ከተማረኩ ባሪያዎች ጋር ይፈቀዳል እነሱ ያገቡም ቢሆኑም እንኳን ነው፡፡ የአንድ ሰው የእንጀራ ልጅ ሚስትንም ማግባት ይፈቀዳል ከተፈታች እንዲሁም ለጋብቻ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ልጆችንም ጭምር 33.37-38፣ 4.23፣ 65.4፡፡

የማያምኑ፡- የማያምኑቱ የመጨረሻውን ፍርድ ክደዋል እንዲሁም ደግሞ ከወላጅ አልባዎች ፊታቸውን መልሰዋል፡፡ እነሱም ሌሎች ድሃዎችን እንዲመግቡ አላበረታቱም፡፡ እነሱም ሃይማኖተኛ መስለው በሌሎች ዘንድ ለመታየት የሞከሩት ናቸው ለተቸገሩትም ምንም ምፅዋትንም አልሰጡም 107.1-7፡፡

ውለታዎች፡- ሌሎች የበለጠ እንዲሰጡ በመገመት (ለውለታ ብላችሁ) አትስጡ 74.6፡፡

ልብስን ማንፃት፡- ልብሳችሁን ንፁህ አድርጉ 74.4፡፡

ትዕግስት፡- አላህ እንዲሰራ አንተ ታጋሽ ሁን 74.7፡፡ ሙስሊም ሁልጊዜ የሚፀልይ እንዲሁም ሌሎች እስላማዊ ሕግን እንዲያከብሩ የሚያደርግ ሕይወት የሚያመጣውን ማንኛውንም ነገር በትዕግስት የሚችል ነው 31.17፡፡

የገንዘብ መዋጮ፡- ሙስሊሞች ለእስልምና ጉዳይ ገንዘብን በቸርነት የማይሰጡ ከሆነ ነፍሳቸውን ይጎዳሉ እንዲሁም ደግሞ በሌሎች ይተካሉ 47.38፡፡

ምስክርነት ከሲዖል፡- ኃጢአተኞች በገነት አትክልት ቦታ በሆኑት ጥያቄን ይጠይቃሉ ‹ወደ ሲዖል ውስጥ ለመላክ ምንድነው ያደረጋችሁት?› መልሱም የሚሆነው እንዳልፀለዩ፣ ድሃዎችን እንዳልመገቡ፣ ሐሜትን እንዳሙና የፍርድ ቀንን እንደካዱ ነው 74.40-46፡፡

ምንም እርግጠኝነት የለም፡- ንስሐ የሚገቡት አነዚያ፣ ለእስልምናም እራሳቸውን ያስገዙቱ እና ትክክል የሆነውን ነገር የሰሩቱ ለዘላለማዊው የአትክልት ቦታ እድል ወይንም ተስፋ አላቸው 28.67፡፡

ተጓዦች፡- ለዘመዶች ለሚያስፈልጋቸው እና ለመንገደኞች የሚገባውን ነገር ስጧቸው 30.38፡፡

የጉዲፈቻ ወንድ ልጆች፡- የሚቻል ከሆነ የጉዲፈቻ ልጆች ስማቸው መጠራት ያለበት በስጋ ወላጆቻቸው ነው 33.5፡፡

እስልምናን መካድ፡- ሙስሊሞች የእስልምና እምነታቸውን እንዲክዱ ቢገደዱ ነገር ግን በልባቸው ቢያምኑ ይቅር ይባላሉ፡፡ ሙስሊም ከሆኑ በኋላ እስልምናን በእውነት የካዱት እነዚያ የአላህን ቁጣ ይቀበላሉ እንዲሁም በጥብቅ ይቀጣሉ 16.106፡፡

የምግብ ክልከላ፡- የተከለከሉ ምግቦች የሞቱ እንሰሳት፣ ደም፣ አሳማ፣ እንዲሁም ለጣዖት የተሰዋ ምግቦች ናቸው ነገር ግን ኃጢአት ለማድረግ ሳይታሰብ ከተበሉ አላህ ይቅር ባይ ነው 16.115፡፡ እነዚህም ከሙስሊሞች በፊት ለመጡት ለአይሁዶችም የተከለከሉ ምግቦች ናቸው 16.118፡፡

መስጊዶችን መጎብኘት፡- ሙስሊሞች ያልሆኑት መስጊዶችን ለመጎብኘት አይፈቀድላቸውም ነገር ግን በአላህና በፍርድ ቀን የሚያምኑት፣ ፀሎታቸውን የሚከታተሉት እንዲሁም ምፅዋትን የሚከፍሉት እና አላህን የሚፈሩት ብቻ ናቸው 9.18፡፡

የማያምኑትን ቤተሰቦች አለመቀበል፡- ሙስሊሞች እስልምናን ላለመቀበል የመረጡትን አባቶቻቸውንም ሆነ ወይንም ወንድሞቻቸው እንደ ወዳጅ ማየትና መቀበል የላባቸውም 9.23፡፡

የፅናት መፈተኛ፡- አላህ ፍርሃትን ረሃብን ሞትን እና የሃብትን ማጣት ሙስሊሞች ይፀኑ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፈተን ይጠቀምባቸዋል 2.155፡፡

አልክሆልና ቁማር፡- የወይን ጠጅ፣ ቁማር፣ ጣዖትን አምልኮ እንዲሁም የወደፊቱን ለማወቅ ቀስቶችን መጠቀም የሰይጣን መሳሪያዎች ናቸው 5.90፡፡

እስላማዊ አገር አቀፋዊነት፡- ሙስሊሞች ፃድቃንና አንድ መንግስት መሆን አለባቸው 3.104፣ 105፡፡ ሙስሊሞች ለሰዎች ልጆች ከተነሱት መንግስታት መካከል ምርጥ መንግስታት ናቸው 3.110፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

በእስልምና እምነት ውስጥ ያለው ሕግ ምን ዓይነትና ከምን እንደመነጨ እንዲሁም በምን ምክንያት እንደተሰጠ ከዚህ በላይ ያነበብናቸው የቁርአን ክፍሎች ግልፅ አድርገዋል፡፡ ከተዘረዘሩትም ውስጥ ብዙዎቹ ማህበራዊና ስርዓታዊ ሕግጋት ናቸው፡፡ ከቅዱስ ፈጣሪ የሞራል ሕግጋት አንፃር የግለሰብ ሕይወት ምን እንደሚጠበቅበትና እንዴት መኖር እንዳለበት፣ የሞራል ሕግጋቱን አለመጠበቅ ከምን የተነሳ ሊሆን እንደሚችል አለመጠበቅም ምን እንደሚያስከትል የሚያመለክቱት ግልፅ ነገር የለም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ግን በዚህ በኩል እጅግ በጣም አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ግልፅ ነው፡፡ ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ የሰው ልጅ ሕይወት በኃጢአት የተበከለ እና የእግዚአብሔርን የሞራል ሕግጋት ማለትም አስርቱ ቃላትን የመጠበቅ አቅምና ችሎታ የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚህም የተነሳ ትልቁና ማዕከላዊው መልእክቱ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቂያውን መንገድ ማሳየት ነው፡፡ አንድ ኃጢአተኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቅ የሚችለው በራሱ በእግዚአብሔር በተዘጋጀው የመታረቂያው መንገድ በኩል እንደሆነ ይገልጣል፡፡ በዚህም መንገድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን ያገኘው ሰው ምህረቱን ያበዛለትን የጌታውን  የሞራል ሕግጋት የሚጠብቅበትን የችሎታ ኃይል እንደሚሰጠውም ይገልፃል፡፡ በጌታ በኢየሱስ ያመኑ ሁሉ ይህንን አግኝተውታል፡፡ በግል ሕይወታቸውም ውስጥ ይህንን የእግዚአብሔርን ፀጋ አግኝተው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት መኖር የየዕለቱ ደስታቸው ሆኗል፡፡ በትክክልም የመንግስተ ሰማይ ወራሾች መሆናቸውንም ተገንዝበዋል፡፡

የዚህ ድረ - ገፅ አዘጋጆችም ትልቅ ጉጉትና መሻት ሙስሊሞች ይህንን እውነታ እንዲገነዘቡና ዘላለምን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ እንዲያሳልፉ ወደ ጌታ ኢየሱስ እንዲመጡ መጋበዝ ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ አግኙና አንብቡ በዚህ ድረ - ገፅ የሚተላለፉትን እውነቶች በመከታተል አንብቡ፡፡ ከጌታ እግዚአብሔር ጋር የመታረቂያው መንገድ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለሰዎች ኃጢአት ዋጋ በከፈለው በጌታ በኢየሱስ በኩል ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፣ ንስሐ በምግባት፣ እግዚአብሔር እንዲቀበላችሁ ባላችሁበት ከልባችሁ ከፀለያችሁ እግዚአብሔር ሊቀበላችሁ፣ ይቅር ሊላችሁና አዲስንም ሕይወት ሊሰጣችሁ ፈቃደኛ ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Islamic Law,  Chapter 3 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ