ጦርነትና ሰላም

M. J. Fisher, M.Div.

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መግቢያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

በዚህ መጽሐፍ ከተካተቱት ሃያ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ይህ በጣም አስፈላጊው ነው ይህም መስከረም 1 ቀን 1994ዓ.ም (9/11 ተብሎ በሚታወቀው) በአሜሪካ ላይ ከተደረገው ጥቃት የተነሳ ነው፡፡ በሰላም እንዲሁም በጦርነት ሐሳቦች ላይ የሚያተኩሩት ዘጠና የቁርአን ጥቅሶች ውስጥ የተሰበሰቡት ሰፊ ዘገባዎች ቀርበዋል፡፡ እያንዳንዱም ጥቅስ በዘመናዊ እንግሊዝኛ ሐሳብ ተገልጧል፡፡ (ከአማርኛው ቁርአን ውስጥ ግልጥ ያልሆኑትን ሐሳቦች ከእንግሊዝኛው ጋር በማስተያየትም ቀርቧል)፡፡

ጦርነትንና ሰላምን በተመለከተ በቁርአን ጥቅሶች ላይ አዝጋሚ የሆነ ለውጥ የሚኖር ከሆነ፣ ሊሆን የሚችለው በዚህ መጽሐፍ በምዕራፍ አንድ ላይ በቁርአን ታሪክ ከተገለፀው የተነሳ መሆን ይኖርበታል፡፡ መሐመድ ለአስር ዓመታት ይህል በመካ ውስጥ ጦርነትን የማይጠቅሱ ጥቅሶችን እያስታወሰ የነበረ መሆኑን እዚህ ጋ እንደገና መድገም በጣም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚያም መሐመድና ተከታዮቹ ወደ መዲና ተሰደዱ በዚያም ጂሃድና ቅዱስ ጦርነት የሚሉት ጥቅሶች መምጣት ጀመሩ፡፡ ጊዜም እቀጠለ ሲሄድ የጂሃድ ጠቃሚነት እየጨመረ ሄደ፣ ስለዚህም በጦርነት ላይ ያሉት ጥቅሶች በጣም ጥብቅ እየሆኑ በቀጣዩ የቁርአን ክፍል ውስጥ ተጠቃለሉ፡፡ መሐመድ ‹ጂሃድን› ሲጠቅስ የተናገረው ሁሉ ለጦርነት እንደነበረ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ላሉት ሙስሊሞች ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ነገር ‹ጂሃድ› መቼ ነው ትክክለኛ የሚሆነው? የሚለው ነው፡፡ መሐመድ በመካ የንግድ ሸቀጥ ተጓዦች ላይ ዘረፋን አዝዞ ነበር፣ እስልምናን እንዲሁም እራሱን የተቃወሙትን እንዲጠቁ አዝዞ ነበር፣ በጦርነቶቹና በጥቃቶቹም ላይ እራሱም ተሳትፎባቸው ነበር ስለዚህም በ625 ዓ.ም. በኡሁድ ጦርነት ላይ ጭንቅላቱ በከፍተኛ ደረጃ ቆስሎ ነበር፡፡

በጦርነት ላይ ትልቅ ትኩረትን ያደረገው መሐመድ በብዙ ምዕራባውያን ዘንድ ይተቻል ይህም  ምንም ዓይነትን ዓመፅን ከማይደግፈው ከጌታ ኢየሱስ ጋር እሱን ሲያነፃፅሩት ነው፡፡ እነሱም በመዲና ውስጥ እጃቸውን የሰጡትን ባኑ ቁሪዛህ የተባሉትን እና 600 እስከ 900 የሚደርሱ ወንዶቻቸው የተገደሉባቸውን እና ሴቶቻቸውና ልጆቻቸው ባሪያዎች የተደረጉባቸውን የአይሁድ ጎሳዎችን ይጠቅሳሉ፡፡ የዚህ ግድያ ከባድነት እጅግ በጣም ዘግናኝ የነበረ በመሆኑ የመሐመድ ጊዜ ጦርነት ወዳድ ጎሳዎች እንኳን በጣም ነበር ያዘኑበት፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ የመሐመድ ጦር የመካ ከተማን በያዘበት ጊዜ ጣዖት አምላኪዎቹና እጅግ በጣም መሐመድን ይቃወሙ የነበሩት አጠቃላይ ምህረት ስለተደረገላቸው እጅግ በጣም ተገርመዋል፡፡

በመሐመድ የሕይወት ዘመን እና በመጀመሪያው የእስልምና መስፋፋት ጊዜ የሙስሊም ጦረኞች ብዙ ድሎችን አግኝተው ነበር፡፡ የእስላማዊው ጦር ዘዴ እስላማዊ ያልሆኑትን አሸብሮአቸው ነበር፡፡ አንዳንድ አገሮች እንደ ኢትዮጵያ እና ሊባኖስ ያሉት ጦራቸውን ተቋቁመውት ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ እስፔን ያሉት የእስላም ተዋጊዎችን ከአገራቸው አስወጥተው ነበር፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ አንዳንድ አገሮች ያለምንም ጦርነት እስልምናን ተቀብለው ነበር ይህም የሙስሊም ነጋዴዎች እምነታቸውን ስላስፋፉት ነበር፡፡

አንዳንድ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስም ዓመፅን ይፈቅዳል በማለት ይናገራሉ፡፡ ነገሩ እውነት ነው፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ልደት በፊት የእግዚአብሔር ሕዝብ በሲቪል ሕግ የሚተዳደሩ፣ የጦር ሠራዊት እና የአገር ድንበር ያላቸው ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በእነዚያ ቀናት እግዚአብሔር አንድን መንግስት በሌላ መንግስት የጦር ሰራዊት ጦርነት አማካኝነት ይቀጣ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእስራኤል መንግስት እጅግ ዓመፀኛ እና የሁሉም ዓይነት ኃጢአት እና ዓመፀኛ ባህል የሞላባቸውን አገር ለመቅጣት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ቅድስቲቱን አገር ለእስራኤላውያን ሲሰጥ የነበረው ሁኔታ ይህንን ይመስል ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ እስራኤል ተሸንፋ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ግዞት ተወስዳለች ይህም በኃጢአታቸው አማካኝነት ለመቀጣት ነበር፡፡ በአይሁዶች ቅዱስ መጽሐፍና በእስላሞች ቁርአን መካከል ከሚገኘው ትልቅ ልዩነት መካከል እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን አይሁዲነት በዓለም መንግስታት ሃይማኖት ሁሉ ላይ የበላይ እስኪሆን ድረስ ጦርነት እንዲያደርጉ ገደብ የሌለው ፈቃድን በፍፁም ያልፈቀደ መሆኑ ነው፡፡   

ክርስትናን አንቀበልም ያሉ አይሁዶች በአባቶቻቸው እምነት የተነሳ በእግዚአብሔር መወደዳቸው ቀጥሏል ሮሜ 11.28-29፡፡ ይሁን እንጂ ክርስትያኖች የሚያምኑት ለብዙ ዘመናት የሚጠበቀው መሲህ ከመጣ በኋላ አስደናቂ የሆነ ለውጥ እንደሆነ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያወጀው የእግዚአብሔር መንግስት በአንድ ቦታ ላይ በፍፁም ሊወሰን እንደማይችል ነገር ግን በተመረጠው ሕዝቡ ልብ ውስጥ እንደሚኖር ነው፣ ማለትም በዓለም አቀፍ ቤተክርስትያን ውስጥ (ይህም ከየሁሉም አገር ዜጋ አማኞች) ማለት ነው፡፡ ክርስትያኖች የሚያምኑት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስትያን እራስ ነበር አሁንም በመሆኑ ይቀጥላል በማለት ነው (ቆላስያስ 1.15-20) ይህም ያለ ድንበር ክልል በምትኖረው ቤተክርስትያኑ ሁሉ ላይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ምህረት የዳኑት ተጨማሪ እርምጃዎችን በማድረግ ጠላቶቻቸውን መውደድና ቀኝ ጉንጫቸውን ለሚመቷቸው ግራቸውን ደግሞ መስጠት አለባቸው፡፡ በዓለም ላይ ያለችው ቤተክርስትያን መለያ ባህርይ ይህ ፍቅር ነው፡፡

ይህ ፍቅር ወንጀለኛ መቅጣትንና ወታደራዊ ጦርነቶች እንዳይደረጉ ይከለክላልን? በክርስትና እምነት ውስጥ የአገር ገዢዎች ስልጣን፣ ወንጀለኞችን ለመቅጣት የሚጠቀሙት ኃይል ወይንም ቅጣት የተከበረ ነው፡፡ በሕግ ማስከበርም ስራ ላይ የተሰማሩትና በጦር ሰራዊትም ውስጥ ያሉት ሁሉ ‹የእግዚአብሔር አገልጋዮች› በመባል ይታወቃሉ፣ ይህም በማህበረሰቡ ውስጥ ስርዓትን ለማስከበር ነው ሮሜ 13.1-7፡፡ ቤተክርስትያንን በተመለከተ ግን ለአዲስ ኪዳን መስፋፋት ምክንያት ‹የጦር ሠራዊት› ጥሪ ወይንም የትጥቅ ጥሪ የሚባል ነገር የለም፡፡ በእርግጥ እጅግ በጣም ብዙ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ማሳሰቢያ በወንድማማቾች መካከል ፍቅርና ምህረት እንዲኖር፣ ጠላቶቻችንንም እንኳን እንድንወድ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ አስደናቂ ፍቅር ከእግዚአብሔር የሆነና በአማኞች ውስጥ በክርስቶስ አማካኝነት የሚሰራ ነው፡፡ ክርስትያኖች ፍቅር የሌላቸው ሆነው ከተገኙ በቅዱስ መጽሐፉ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አልታዘዙም ማለት ነው ሮሜ 12.14-21፡፡

ብዙ ሙስሊሞች ክሩሴድን የቤተክርስትያን የዓመፅ ድርጊት ነው በማለት ለማስጃነት ይጠቁማሉ፡፡ በክሩሴድ የጦር ኃይል ዘመቻ ወቅት ስነ-ምግባራዊ ያልሆኑ ብዙ ነገሮች ተከስተው የነበረ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ሊቃውንት ክሩሴዶችን፣ በታሪክ የነበሩ የጨለማ ዘመኖች ብለው ጠርተዋቸዋል፡፡ የሙስሊም ኃይላት የክርስትያን አገሮችን ለዘመናት ሲያጠቁ ኖረዋል፡፡ የእነሱ ጦርነት የቅድስት ምድር እስራኤልንም ጨምሮ ነበር፡፡ ለክሩሴድ መነሻ የሆነው ምክንያትና ስረ መሰረቱ፣ ሙስሊሞች የክርስትያን ቅዱስ ቦታዎችን አረከሱ፣ ወደ ቅድስ አገር ጉዞ የሚያደርጉትን ክርስትያኖች አሳደዱ የሚለው ሪፖርት ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ጦረኞች ቃለ መሐላን ያደረጉት በ1095 ዓ.ም ፖፕ አርባን ሁለተኛው፣ ቅድስተ አገርን ከመሐመዳውያን ነፃ ለማውጣት ጦር ሠራዊትን ባደራጀ ጊዜ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ጦረኞች (ክሩሴደሮች) ከተልእኮአቸው አልፈው በመሄድ ክርስትያናዊ ስነ-ምግባራቸውን ጥሰው ምድራዊ በቀልንና ንብረት ፍለጋ ላይ በማተኮራቸው ነበር፡፡ ምንም ይሁን ምን የእነሱ ጭከና በክርስቶስ ወንጌል የተነሳሳ አልነበረም፡፡

ብዙ ሙስሊሞች በዓለም ታሪክ ውስጥ ሁሉ በእስልምና ስም ስለተደረጉት እጅግ ብዙ ጭከናዎች ተመሳሳይን ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ እነሱም ቁርአን የሰላም ሃይማኖት ነው በማለት ስለሚያስተምር በማለት ይናገራሉ፡፡ ለማስረጃም ያህል እጅግ በጣም ብዙ የእስላም አገሮች መስከረም 9/11 ጥቃት ላይ ተመስርቶ በአሸባሪዎች ላይ በሚደረገው ጦርነት ተባባሪዎች ናቸው በማለት ሊጠቅሱ ይችላሉ፡፡ ለመሆኑ ቁርአን የአሻባሪ ተግባራትን ይደግፋል ወይንስ ‹ጂሃድ› የተወሰነው እራስን በመከላከል ተግባር ላይ ብቻ ነው? የሚቀጥለው ርዕሳዊ ጥናት እናንተው ለራሳችሁ ለዚህ የሚሆንን መልስ እንድትወስኑ ይረዳችኋል፡፡

ቁርአን የሚከተለውን ይናገራል፡-

ለጂሃድ መግቢያ፡- እነዚያም ያመኑት ሰዎች (መታገል ያለባት) ሱራ አትወርድም ኖሮአልን? ይላሉ፣ ነገር ግን ጦርነትን የሚገልጥ አንድ ሱራ በወረደ ጊዜ፣ ደካማዎቹ ወደ መሐመድ በሞት ፍርሃታቸው ውስጥ ሆነው በመዛል ይመለከታሉ 47.20፡፡

አላህ ጦረኞችን ይወዳል፡- አላህ ለእስልምና የሚዋጉትን ልክ እንደ ተናሰ ግንብ ሆነው የሚሰለፉትን ይወዳል 61.4፡፡

ቤተክርስትያናትን መጠበቅ፡- ብዙ ገዳማትን፣ ቤተክርስትያናትን፣ ምኩራቦችን እና መስጊዶችን ከመደምሰስ ለማዳን አላህ አንድን ሕዝብ ከሌላው ጋር እንዲዋጋ በማድረግ ይጠብቃል፡፡ በእነዚህ በእያንዳንዳቸው የአላህ ስም በየዕለቱ ይወሳባቸዋል 22.40፡፡

ተቃዋሚዎችን መግደል፡- ሙስሊሞች የሚቃወሙዋቸውን የማያምኑትን መዋጋት አለባቸው፡፡ ሙስሊሞች የእስልምናን የጦርነት ሕግ መታዘዝ አለባቸው፡፡ የማያምኑትን ባገኙበት ቦታ ላይ ሁሉ መግደል አለባቸው፡፡ ከሙስሊሞች ላይ ከወሰዱት አገር ውስጥ ማስወጣት አለባቸው፡፡ ከማያምኑት ዘንድ (በሙስሊሞች ላይ የሚመጣውን) የሆነውን ችግርና መከራ መቻል ከመግደል ይልቅ እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው 2.190-191፡፡ ሙስሊሞች በበዓል ቀን እንዲዋጉ ተፈቅዶላቸዋል የጣዖት አምላኪዎችን መግደል፣ ሙስሊሞች ከእነሱ ከተቀበሉት ስቃይ የተነሳ ፍትሃዊ ነው 2.217፡፡

ለእስልምና መዋጋት፡- ሙስሊሞች ጦር የሌላቸው ወይንም በደንብ ያልታጠቁም እንኳን ቢሆኑ ለአላህ ሲሉ ወደ ጦርነት መዝመት አለባቸው 9.41፡፡ ለሙስሊሞች እራሳቸውንና ሃብታቸውን ለእስልምና ሲሉ መስጠታቸው አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም በገነት ውስጥ ሽልማት ይኖራቸዋልና፡፡ በዚህም ዓለም እንኳን ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ (ከሰማይም) ለፈጣን ድል ከላይ የሚመጣ እርዳታ ይኖራል፡፡ ይህንን መልካም ዜና ለታማኞቹ አሰራጩት፡፡ አማኞች የአላህ እረዳቶች ሁኑ የኢየሱስ ደቀመዛምርት እንዲህ ዓይነት ነበሩ እነሱም በሌሎች በማያምኑት እስራኤላውያን ላይ እርዳታን አግኝተው ነበር፡፡ እነሱም በጣላቶቻቸው ላይ ድልን ተቀዳጅተው ነበር 61.10-14፡፡

ድህረ ጦርነት ስቃይ፡- ከድል በፊት በጦርነት ላይ የተሳተፉትና የገንዘብንም እርዳታ ያደረጉት ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ እና ድሉ ከታወቀ በኋላ እርዳታ ካደረጉት ይልቅ ታላቅ ከበሬታን ያገኛሉ 57.10፡፡

የጦር ሜዳ መመሪያዎች፡- ከማያምኑት ጋር በተጋጠማችሁ ጊዜ ጦራችሁን የምታልሙት በአንገታቸው ላይ ነው፡፡ ጦርነቱን በድል ካጠናቀቃችሁ በኋላ የተማረኩትን አጥብቃችሁ እሰሯቸው፡፡ ከዚያም ለእስረኞቹ መሐሪ ልትሆኑላቸው ትችላላችሁ ወይንም ነፃነት እንዲወጡ ክፍያ ልትጠይቁ ትችላላችሁ 47.4፡፡

የገነት ብቸኛው እርግጠኝነት፡- ወታደሮች ለእስልምና በመዋጋት ላይ እያሉ በጦርነት የሞቱት ወደ ገነት ወይንም ወደ ዘላለማዊው የገነት ቦታ የተስፋ ቃል ተገብቶላቸዋል 47.4-6፣ 3.169-171፡፡

የጦርነት ምርኮዎች፡- ከከተሞች የጦር ምርኮዎች ሆነው የተወሰዱት ነገሮች መከፋፈል ያለባቸው በሃብታሞች መካከል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እነሱም ለመሐመድና ለድሆች ይሰጣሉ፡፡ መሐመድም እነሱን እንደሚገባ አድርጎ ያከፋፍላቸዋል ማንም ሰው ማጉረምረም አይኖርበትም 59.7 እና 8.1፡፡ ሙስሊሞች የሌሎችን ንብረት ለመውሰድ በሚሄዱበት ጊዜ አንዳንድ ለመዋጋት የማይበቁ ለመዋጋት እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፣ ነገር ግን መሐመድ የሚነግራቸው እነሱ እንደማይሳተፉበት ነው 48.15-16፡፡ ሙስሊሞች ገና ያልወሰዱትን ሌሎች ዝርፊያዎችን አላህ ያውቃል 48.18-21፡፡ በጦር ምርኮም ደስ ይበላችሁ 8.69፡፡

በሙስሊሞች መካከል ጦርነት፡- በሙስሊሞች መካከል ጦርነት ቢነሳ እያንዳንዱ ትክክል ያልሆነው ክፍል እጅ እስከሚሰጡ ድረስ መዋጋት አለበት ከዚያም ሚዛናዊ ሁኑላቸው 49.9፡፡

የድል የተስፋ ቃል፡- ለሙስሊም ተዋጊዎች በጣም ብዙ ምርኮ ንብረትና ፈጣን ድል የተስፋ ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጠላቶቻቸው ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ የማያምኑት ሙስሊሞችን ለመውጋት ቢመጡ ያለምንም አጋዥ ወይንም እርዳት ወደ ኋላቸው ያፈገፍጋሉ የሚጠብቃቸውም ምንም የለም 48.20-22፣ 8.7-10፡፡ አላህ ያላቸው እነዚያ ብቻ መሐመድና ታማኝ የሆኑት ሙስሊሞች እንደ ጓደኞቻቸው ማሸነፋቸው እርግጠኛ ነው 5.56፡፡ ድልም የሚመጣው ከአላህ ብቻ ነው 3.126፡፡

ሙስሊሞች ጨካኞች ናቸው፡- መሐመድን የሚከተሉት በማያምኑት ላይ ጨካኞች ሲሆኑ እርስ በእርስ ግን ርህሩህ ናቸው፡፡ 48.29፡፡

ፍርሃት፡- ከሙስሊሞች ጋር በተደረገው ጦርነት ላይ እርዳታን ያደረጉት አይሁዶች ከምሽጎቻቸው ውስጥ በተዓምር ወጥተው ፈርተዋል፡፡ ለዚህ ነው ሙስሊሞች ሊገድሏቸው ወይንም ሊማርኳቸው የቻሉት፡፡ ሙስሊሞችም የአይሁዶች ምድር፣ ቤቶችንና ንብረቶችን ገዢዎች (ተቆጣጣሪዎች) ሆነዋል 33.26-27፡፡ እጅግ ብዙ ሰዎችንና የጦር መሳሪያዎችን ሰብስቡ ከዚያም በጠላቶቻችሁ ልብ ውስጥ ፍርሃትን ታስቀምጣላችሁ 8.60፡፡

እራስን ቁረጡና በከፍተኛ ደረጃ አቁስሉ፡- የማያምኑት ልቦች በጣም መሸበር አለባቸው ስለዚህም ሙስሊሞች በጀግንነት ማጥቃት እራሶችን መቁረጥ እንዲሁም ጣቶቻቸውን ሁሉ መቁረጥ አለባቸው፡፡ ምርኮኞቹን በጣም ማቁሰል ማለት አላህን እና መሐመድን የሚቃወሙት ውጤት ከባድ ቅጣት መሆኑን ያሳያል፡፡ እነሱም ወደ ሲዖል ይሄዳሉ 8.12-14፡፡

የጠላቶች አያያዝ፡- በአላህ እና በመሐመድ ላይ ጦርነትን ያደረጉት እነዚያ መገደል፣ መሰቀል እጅና እግራቸው በተቃራኒ ጎን (ግራ እጅ ቀኝ እግር፣ ቀኝ እጅ ግራ እግር) መቆረጥ አለባቸው ወይንም መሰደድ አለባቸው፡፡ በዚህ ምድር መዋረድ ከሞት በኋላ ደግሞ መጥፋት አለባቸው 5.33፡፡ እነሱም ሙስሊም እንዲሆኑ መገደድ የለባቸውም 2.256፡፡

ለፈሪ ሙስሊሞች ሞት፡- ሙስሊሞች የማያምኑትን በጦርነት ላይ ሲገጥሙ ለስልታዊ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ማፈግፈግ የለባቸውም፡፡ ከፍርሃት የተነሳ የሚመለስ ማንም ቢኖር እሱ መቀጣት አለበት የእሱም ቤት የሚሆነው ሲዖል ነው 8.16፡፡

በማያምኑት ላይ ጦርነትን አድርጉ፡- ሙስሊሞች የማያምኑትን መዋጋታቸውን መቀጠል አለባቸው ይህም የእስልምና ሃይማኖት በሁሉም ቦታ ላይ ዋና እስከሚሆን ድረስ ነው 8.39፡፡ በማያምኑት ላይ ጦርነትንና መጥፎ ነገርንም አድርጉባቸው፡፡ የእነሱም የሐዘን የጉዞ መጨረሻ የሚሆነው ሲዖል ነው 9.73፣ 66.9፡፡

ስምምነቶችን አፍርሱ፡- ከማያምኑት ጋር የገቡትን ስምምነት ሙስሊሞች ማፍረስ ይችላሉ ይህም የማያምኑት አጭበርባሪዎች ናቸው የሚል ስሜት ከተሰማቸው ነው፡፡ የማያምኑት ለሙስሊሞች ምንም መልካምን ነገር ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ እነሱም እጅግ በጣም እንዲፈሩ ኃይለኛ በሆነ ኃይል መወጋት አለባቸው ነገር ግን እጅ መስጠት ከፈለጉ ከዚያም ከእነሱ ጋር ሰላምን አድርጉ 8.57-61፡፡

ሙስሊሞች ሁልጊዜ ድል አድራጊዎች ናቸው፡- አንድ መቶ የሚሆኑ ጥሩ ሙስሊሞች ቢኖሩ እነሱ የማያምኑትን ሁለት መቶ ሰዎች ይወጋሉ፡፡ አንድ ሺ ቢኖሩ ደግሞ ሁለት ሺዎች ከፊታቸው ይሸሻሉ ምክንያቱም እነሱ ምንም እውቀት የላቸውምና 8.66-67፣ 3.126፡፡

እስረኞች፡- በሚወጉት ምድር ላይ የመጨረሻ ድል እስከሚገኝ ድረስ መሐመድ የጦር እስረኞችን መያዝ የለበትም፡፡ ሙስሊሞች የጦር ምርኮን በቶሎ ይፈልጋሉ ምክንያቱም ከሰማያዊ ሽልማት ይልቅ ምድራዊ ሽልማትን ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ሙስሊሞች መደሰት ያለባቸው በጦርነት ባገኙት መልካምና ሕጋዊ በሆኑት ነገሮች ነው፣ ነገር ግን ሕጋዊ ያልሆኑ ሃብቶችን በማግኘት ለመደሰት መሞከር የለባቸውም 8.67-69፡፡

ቅምጦች፡- ያገቡ ሴቶችን ማግባት ለሙስሊሞች ክልክል ነው፣ ይህም እነሱ በጦርነት ኃይል ያገኟቸው የራሳቸው ባሪያዎች ካልሆኑ በስተቀር ነው 4.24፡፡ ሙስሊሞች ከሚስቶቻቸው ወይንም በጦርነት ከያዟቸው ከባሪያዎቻቸው ውጪ የግብረ ስጋ ግኑኝነትን ከማድረግ የተቆጠቡ ናቸው፡፡ ከእስረኞች ጋር የሚደረግ እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ምንም ስህተት የለበትም 23.5-6፡፡ ባሪያዎች ለጌቶቻቸው አላህ ከሰጠው ሃብት እኩል አይካፈሉም፡፡ ጌቶቻቸውም ሌሎች ሙስሊሞችን እንደሚፈሩት ባሪያዎቻቸውን ሊፈሩ አይገባቸውም 30.28፡፡

ጣዖት አምላኪዎችን ግደሉ፡- ከጦርነት የሚታረፍበት ቀን ካለቀ በኋላ ሙሽሊሞች ባገኙበት ቦታ ሁሉ ላይ ጣዖት አምላኪዎችን ይገድላሉ፡፡ እነሱንም ይይዟቸዋል ይከቧቸዋል እነሱንም ለማጥቃት ባገኙበት ቦታ ሁሉ ያደፍጣሉ፡፡ እነሱም ወደ እስልምና እምነት ከተመለሱ፣ ከፀለዩ እና ምፅዋትንም ከሰጡ ያን ጊዜ እነሱ እንዲኖሩ ይፈቀድላቸዋል 9.5፡፡

በዓመቱ ሁሉ ውስጥ ጦርነትን አድርጉ፡- አላህ አስራ ሁለት ወራትን ፈጥሯል ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ቅዱሳን ናቸው፣ ነገር ግን የማያምኑት በአስራ ሁለቱም ወራት ውስጥ ስለሚዋጉ ለሙስሊሞችም በአስራ ሁለቱም ወራት ውስጥ ከጣዖት አምላኪዎች ጋር እንዲዋጉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ 9.36፡፡

ከማንኛውም ሰው ጋር መዋጋት፡- ሙስሊሞች እስልምናን የተቃወመውን ማንኛውንም ሰው ይዋጋሉ፣ እስልምናን ከተቃወሙ ከክርስትያኖችም ከአይሁዶችም ጋር እንኳን ቢሆን፡፡ ይህም እነሱ መደበኛ የገንዘብ መዋጮች እስከሰጡ ድረስ እራሳቸውንም ሙሉ ለሙሉ ለሙስሊም ተዋጊዎች እስካስገዙ ድረስ ነው 9.29፡፡

ሃይማኖቶችን በሙሉ አሸንፉ፡- አላህ መሐመድን የላከው ከእውነተኛ ሃይማኖት ጋር ነው ስለዚህም ከሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ይልቅ (እስልምና) የበለጠ እንዲሆን ነው 9.33፡፡

ግደሉ እና ተጋደሉ፡- ለሕይወታቸውና ለአደረጉት አስተዋፅዖ ሙስሊሞች የገነት አትክልት ቦታን ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም የተስፋ ቃል የተሰጠው ስለ እስልምና ለሚዋጉት፣ ለሚገድሉትና ለሚጋደሉት ነው፡፡ ይህም ተመሳሳይ መልክት በቶራህም፣ በወንጌል እና በቁራን ውስጥ ይገኛል 9.111፡፡

ጎረቤቶቻችሁን ተዋጉ፡- ሙስሊሞች በአካባቢያቸው ከሚኖሩ ከማያምኑት ጋር ጦርነትን ያደርጋሉ እነሱም በእነሱ ላይ ክፋትን ማሳየት አለባቸው 9.123፡፡

የናድር አይሁዶች ምሳሌ፡- በመጀመሪያው ጥቃት ላይ የመጽሐፉ ሰዎች መሸነፍ የአላህ ስራ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ሙስሊሞች (የናድር አይሁዶች) በፍርሃት ቤታቸውንና ትተው ይሄዳሉ በማለት አላሰቡም ነበር፡፡ አላህ የእነሱን ንብረት ለመሐመድ ሰጠው እሱም እንደፈቀደ አከፋፈለው፡፡ አንዳንድ ግብዞች አረቦች መሐመድ የመጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች ከአጠቃቸው እና ከንብረታቸው ላይ ካወጣቸው እንደሚረዷቸው ቃል ገብተውላቸው ነበር ነገር ግን እነሱ ዋሽተዋል፡፡ እነሱም ከሰይጣን ጋር ወደ ሲዖል ይሄዳሉ 59.1-17፡፡

ተለወጡ ወይንም ተገደሉ፡- ግብዞቹና ችግር ፈጣሪዎች በከተማ ውስጥ ካልተለወጡ አላህ ሙስሊሞችን አስነስቶ በየትም ባገኙበት ቦታ ላይ ያለምንም ምህረት ይይዟቸዋል ይገድሏቸዋልም 33.60፣61፡፡

ከሰይጣን ጓደኞች ጋር ተዋጉ፡- እውነተኛ ሙስሊሞች ስለ አላህ ይዋጋሉ የማያምኑት ግን የሚዋጉት ለጣዖቶቻቸው ሲሉ ነው፡፡ እነዚህን የሰይጣን ጓደኞችን ተዋጓቸው 4.76፡፡

ለዝርፊያ ስትሉ አትግደሉ፡- ምርኮን ለማግኘት ሲሉ፣ ሰላምንም ተጠይቀው እንኳን ሙስሊሞች ይገድላሉ፡፡ ይህንን ስራቸውን አቁመው ልዩነትን ማድረግ አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት እንደዚህ ስላደረጉ አላህ ይቅር ብሏቸዋል ነገር ግን አላህ ስለ ወደፊቱ ነገር አዋቂ ነው 4.94፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

ብዙ ሙስሊሞች እስልምና የሰላም ሃይማኖት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የሙስሊሞች መጽሐፍ ቁርአን ግን በጦርነት እና በግድያ የተሞላ ነው፡፡ እንዲያውም እምነቱን በመከተል መንግስተ ሰማይ ወይንም ገነት መግባት እንደሚቻል ተስፋ ከመስጠት ይልቅ በጦርነት ላይ መጋደል ወይንም መሞት የገነት መግቢያ ዋስትና አድርጎ አቅርቦታል፡፡

ሙስሊሞች የሚያመልኩት እውነተኛውን እግዚአብሔር ከሆነ ይህ የቁርአን አመለካከትና ትምህርት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ የክርስትያኖች የእምነት መመሪያ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን ከዚህ በጣም የተለየ ሐሳብን ነው፡፡ ክርስትያኖች ወዳጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻቸውንም እንዲወዱ መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል፡፡

ይህንንም የሚያደርጉት እግዚአብሔር ወዷቸው ስለተቀበላቸውና ምህረትንና ቸርነትን ስላደረገላቸው ነው፡፡ በምህረቱ የተነሳ የዘላለምን ሕይወት አግኝተዋል ይህም እርግጠኛ እንደሆነ ያውቃሉ ስለዚህም በምድር ላሉት ለሚጠሏቸውም እንኳን ይህንኑ እውነት ይገልጣሉ፡፡ ታዲያ የትኛው ነው እውነተኛና የሰላም ሃይማኖት ሊባል የሚችለው? ይህንን ጥያቄ አንባቢዎች እንዲያስቡበት ስንተወው፣ በአንፃሩ የምንጋብዛቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማግኘት እንዲያነቡና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው ዋና ነገር ምን እንደሆነ እንዲያስተውሉ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው ሐሳቡ ግለ ሰቦች ከሕያው እግዚአብሔር ጋር ስለሚታረቁበት የደኅንነት መንገድ መግለጥና ይህንንም ማሳወቅ፣ ማወጅም ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሁሉ በኃጢአተኝነታቸው የተነሳ ከእግዚአብሔር እጅግ እንደራቁና የእግዚአብሔር የፍርድ ቁጣ በላያቸው ላይ እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ ከሕያውና ከዘላለማዊ፣ ከቅዱስ ፈጣሪ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና መንግስቱን መውረስ የሚችሉት እራሱ እግዚአብሔር ባዘጋጀው መንገድ ብቻ ነው፡፡ እሱ ሰዎችን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸውን አዳኙን ሰጥቷል፡፡ እሱ በሰራው ስራ ማመንና በእሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር መምጣት ነው ብቸኛው የደኅንነት መንገድ፡፡

ይህንን አስደናቂ እውነት በመገንዘብ የብዙዎች ሕይወት ፍፁም ተለውጧል ተስፋቸው ለምልሟል የመንግስተ ሰማይ ወራሽ መሆናቸው ተረጋግጦላቸዋል፡፡ የዚህ ገፅ አዘጋጆችም ዋና ሐሳብ ይህንን እውነት አንባቢዎች ለራሳቸው እንዲያገኙ ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን እንድታገኙ፣ እንድታነቡ፣ በዚህም ገፅ ላይ የሚወጡትን አንቀፆች በጥንቃቄ እንድትከታተሉና ነፍሳችሁን ሊያድን ወደሚችለው ብቸኛው አዳኝ ወደ ጌታ ኢየሱስ እንድትመጡ ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Warfare and Peace,  Chapter 3 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ