ተፈጥሮና ሳይንስ በቁርአን

M.J Fisher, M.Div.

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

መግቢያ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማነፃፀሪያ

በቁርአን ውስጥ የተፈጥሮ ታሪክ ይኖራልን? ይህንን እውነት አጠቃሎ ለመናገር የሚችል አንድ እረጅምና የተሟላ አንቀፅ በቁርአን ውስጥ የለም፡፡ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ እንዳለው ማለት ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ የሚገኙት እና ፍጥረትን በተመለከተ የሚናገሩት ጥቅሶች በቁርአን ውስጥ፣ ውስጥ ውስጡን ተበትነዋል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አንድ መቶ አርባ ዘጠኝ ጥቅሶች ተለቅመውና ተደራጅተው አጫጭር መግለጫ ተሰጥቶአቸዋል፡፡ በመሆኑም ፈጣን መምሪያን እንዲሰጡ ቀርበዋል ይህም በፍጥረተ ዓለም (በዩኒቨርስ)፤ በምድር እና በሰው ልጅ አፈጣጠር ላይ እስልምና የሚያስተምረውን ለማሳየት ነው፡፡

በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስና በእስልምና ዘገባዎች መካከል ጥቂት የሆኑ መመሳሰሎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌም ያህል መጽሐፍ ቅዱስና ቁርአን ፀሐይን ትወጣለች ደግሞም ትጠልቃለች ብለው ይናገራሉ፡፡ ይህም በዘመናዊውም ጊዜ እንኳን የአንድ ቀንን ማለፍ የሚናገር የተለመደ አገላለጥ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለነዚህ እውነታዎች ከሚናገረው በላይ ቁርአን አልፎ በመሄድ ስለፀሐይና ጨረቃ ተጨማሪ ነገሮችን እንዲሁም ድርጊቶችንም ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ታላቅ ሰው ፀሐይን በጭቃማ ኩሬ መሳይ መሬት ስትጠልቅ በሩቅ ምዕራብ እንዳያት ይናገራል፡፡ በተጨማሪም ቁርአን ፀሐይና ጨረቃ ምድርን እንደሚዞሩና አንዳቸውም ሌላቸውን መቅደም እንዳይችሉ መከልከላቸውን ይናገራል፡፡

በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌሎችም ልዩነቶች ይገኛሉ፡፡ አንዱም ምሳሌ የሚሆነው ተራራዎችን በተመለከተ የሚናገሩት ነው፡፡ ምድር በውሃዎች እንዴት ተሸፍና እንደነበርና ደረቁ መሬት ከባሕር ውስጥ እንዴት እንደተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር፣ ቁርአን ግን ተራራዎች በመሬት ላይ የተቀመጡት ምድርን ከመንሸራተት እንዲጠብቁ ነው ይላል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ጥቅስ የሚገልፀው ፀሐይና ጨረቃ ከአጠቃላይ ሰማይና ምድር ጋር እንዴት እንደተፈጠሩ ነው፤ ነገር ግን ጊዜዎችን ለመጠቆም ስለመፈጠራቸው ከአራተኛው ቀን በፊት አይናገርም፡፡ የክርስትያን የተፈጥሮ ተመራማሪዎች ይህ የሆነበት ምክንያት ምናልባትም ምድርን የከበባት ጥቅጥቅ ያለ ደመና ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለው ይናገራሉ፡፡ ቁርአን የሚናገረው ፀሐይና ጨረቃ የተፈጠሩት ምድር ከመፈጠሯ በኋላ እንደሆነ ነው፡፡ ቁርአን በመቀጠልም የሚገልጠው እነሱ በሰማይ ክበብ (ዶም) ላይ እንደ ብርሃን እንደተንጠለጠሉ ነው፡፡

ቁርአን በመቀጠልም የሚጨምረው መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተወርዋሪ ኮከቦች ምንም የሚናገረው ነገር የለውም ቁርአን ግን የሚገልጠው ተወርዋሪ ኮከቦች ጅኒዎችን ለማባረር የሚተኮሱ ሚሳየሎች ናቸው የሚተኮሱትም ጅኒዎች ከሰማይ ክበብ በላይ ባለው በእግዚአብሔር ዙፋን ማለትም አላህ ባለበት ቦታ የሚሆነውን ነገር እንዳይሰሙ ለማድረግ ነው ይላል፡፡ (ቁርዓን የሚያስተምረው ነገር ጅኒዎች መንፈሳዊ አካላት ናቸው ምናልባትም ከአጋንንት ጋር ይመሳሰላሉ ይሁን እንጂ ሁሉም ክፉ መናፍስት አይደሉም፡፡ እነሱም ነፃ ፈቃድ እንዳላቸው እና አንዳንዶቹም ሙስሊሞች እንደሆኑ ነው)፡፡

ቁርአን ስለ ምድር አፈጣጠር ያለው አስተምህሮ በመሐመድ ዘመን የነበሩት አረቦች ከነበራቸው መረዳት ጋር በጣም የተመሳሰለ ነው፡፡ በመሆኑም በምንም መንገድ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በፍፁም ሊሄድ አይችልም፡፡ ሙስሊም ያልሆነ አንባቢ የሙስሊም አስተማሪዎች ከዚህ በታች የሰፈሩትን ጥቅሶች አሁን ስለ ዩኒቨርስ ካለው መረዳት ጋር እንዴት ማስታረቅ እንደሚችሉ ያለባቸውን ችግር ማድነቅ ይገባዋል፡፡

ተፈጥሮንና ሳይንስን በተመለከተ ቁርአን የሚከተለውን ይናገራል

ስድስት ቀናት፡- ፈጠራው የተጠናቀቀው በስድስት ቀናት ነው 10.3፡፡

ስርዓት፡- ምድር በአራት ቀናት ተጠናቀቀች፡፡ ከዚያም እስከዚያ ድረስ ገና ጭስ ለነበረው ለሰማይ ትኩረት ተሰጠው፡፡ በሁለት ቀናት ሰባት ሰማያት ተፈጠሩ የታችኛው ሰማይ በብርሃን ተሞላ 41.10-12፡፡ በምድር ላይ ማንኛውም ነገር የተፈጠረው አላህ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ወይንም ወደሰማይ እና ሰባት የሰማይን ደረጃዎችን እስኪያስተካክል ድረስ ነው 2.29 41.10-12፡፡

ጠፍጣፋ ምድር፡- በቁርአን የፍጥረት ዘገባ መሠረት ምድር ጠፍጣፋና ዝርግ ናት ወይንም የተዘረጋች ናት 88.20፤ 15.19፤ 79.30፡፡ አላህም በሰዎች ስር ዋሻ እንድትሆን አይፈቅድላትም 67.16፡፡ ሁለቱም ምድርና ሰማይ የአላህ ደጋፊ ኃይል ባይኖር ኖሮ ይወድቁ ነበር፡፡ ቢወድቁም ኖሮ ማንም ሰው ሊመልሳቸው አይችልም ነበር 35.41፤ 16.45፡፡

ተራሮች በምድር ላይ ተቀመጡ፡- ጠፍጣፋዋን ምድር ከመንቀሳቀስ እንዲያግዷት ተራራዎች እንደ ግዙፍ የማይነቃነቅ ክብደት ወይንም ችካል (ምሰሶ ሆነው) ተደርገው በምድር ላይ ተቀምጠዋል 15.19፣ 21.31፣ 31.10፣ 88.19፣ 16.15፣ 79.32፣ 78.7፡፡

ሰው፡- ሰው የተፈጠረው በጭንቀት ውስጥ እንዲሆን ነው 90.4፡፡ ሰው በመጀመሪያ የተፈጠረው ከሸክላ ነበር፡፡ እሱም ከዚያ የተፈጠረው እንደ ሸክላ ነገር ሆኖ ነበር ከዚያም ሕይወት ያለው ነገር (ጀርም) ሆኖ በማህፀን ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ጀርሙም ወደ ረጋ ደምነት ተቀየረ፡፡ የረጋውም ደም ወደ ትንሽ ስጋነት ሆነና ወደ አጥንትነት ተቀየረ፡፡ አጥንቱም ከዚያ በስጋ ተሸፈነ፡፡ ይህ አስደናቂ የዕድገት ሂደት ነው በዚህም ነው ሕይወት የሚፈጠረው እንደገናም የሚፈጠረው 23.12-14፡፡ እያንዳንዱ ሰው የጀመረው እንደ ሚፈስ የወንድ ፈሳሽ ሆኖ ነው ይህም ወደ ረጋ ደምነት ተቀይሮ የወንድና የሴት አካል ክፍለነት ይለወጣል 76.37-39፡፡

ሴት፡- ለወንድ ጓደኛ የምትሆን ተፈጠረች በእሷም እሱ መፅናናት እንዲያገኝ ነው ይህም በእሷ ሲያርፍና ልጆችን ሲያገኝ ነው 7.189፡፡ ወንዶች የተፈጠሩት በሴቶች ላይ የበላይነት ኖሯቸው ነው ማለትም እነሱ በሴቶች ላይ ስልጣንን እንዲለማመዱ ሆነው ነው እነሱም ዓመፀኞች ሆነው ከተገኙ ሊመቷቸው ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ሴቶች ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ ሁሉ በወንዶች ላይ መታመን የሚኖርባቸው 4.34፡፡

ሰማይ ክብ ቅርፅ ነው፡- ሰማይና ሰማያት፣ ተራራዎችና ሕይወት ያላቸው ነገሮች ተፈጥረው ከተጠናቀቁ በኋላም እንኳን አሁንም ገና ጭስ ነበሩ 41፡1-11 እና 2.29፡፡ ሰማይም ተገንብቶ የነበረው በምድር ላይ እንደ ዶም (ክብ ቅርፅ) ሆኖ ነበር 2.22፣ 21.32፡፡ እሱም ልክ እንደ መሸፈኛ በላይ ከፍ ብሎ ተነስቶ ነበር 79.28፡፡ አስደናቂነቱ እንዳለ ነው የቀጠለው ምክንያቱም የሚታይ ምሰሶና ምንም ስንጥቅ የለውምና 31.10፤ 50.6፡፡ እሱም የተገነባውና ተውቦ የነበረው በሚያብረቀርቁ ጌጣጌጦች ሲሆን ምንም ስንጥቅና ምንም እንከን የለውም 50.6፡፡ እሱም ልክ እንደ ሰማይ ቁራጭ በአንድ ሰው ላይ ለፍርድ ቅጣት እንደሚወድቅ እንደ ማስፈራሪያ ሆኖ ይኖራል 34.9፡፡

ከዋክብት እንደ መብራት (እንደ ፋኖስ)፡- ከመሬት በላይ ሰባት የሰማይ ደረጃዎች ተገንብተዋል እነዚህም ከመውደቅ በተዓምራት ተጠብቀዋል፡፡ የታችኛውም ክፍል በሚያበሩ ብርሃኖች ተጊጦአል 41.12፤ 67.5፡፡

የዞዲያክ ምልክቶች፡- ሰማይ በዞዲያክ ምልክቶች በጣም እንዲያምር ተደርጎ ተጊጧል 15.16፤ 25.61፡፡

በራሪ ከዋክብት ሰይጣናትን ያባርራሉ፡- በራሪ ከዋክብት ለተለየ ዓላማ ነው የተፈጠሩት፡፡ እነሱም በሰማይ የሚከናወነውን ነገር ለመሰለል ወደ ሰማይ በሚበሩት ጂኒዎች ላይ እንደ እሳት ሚሳየል ሆነው የሚወረወሩ ብርሃኖች ናቸው 37.6-10፤ 15.17-18፤ 67.5፤ 26.210-212፡፡

ሰይጣን፡- ከሰዎች መፈጠር አስቀድሞ ሰይጣን ጭስ ከሌለው እሳት ውስጥ ተፈጠረ፡፡ እሱም ከሸክላ ተገንብቶ ሕይወት እንዲኖረው ለተደረገው ለአዳም እንዲሰግድ የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወሙ ተፈረደበት፡፡ እሱም ሲጠፋና ወደ ምድር ሲዋረድ ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት መሐላን ማለ፡፡ አዳምና ሔዋንም የእሱ የመጀመሪያ የጥፋቱ ተጎጂዎች ሆኑ፡፡ እሱም ከጂኒዎች አንዱ ነበረ 15.28-39፣ 7.11-23፣ 18.50፡፡

ክፉ መናፍስት፡- ጂኒዎች የተሰሩት ጭስ ከሌለው እሳት ነበር 55.15፡፡

ፀሐይ ጨረቃና መሬትን መዞር፡- ሰባቱ ሰማያት በምድር ላይ ከተገነቡ በኋላ ፀሐይ እንድታገለግል ተደረገች 13.2-3፣ 78.12-13፡፡ ፀሐይ የምታበራ መብራት (ሻማ ወይንም ፋኖስ) ናት 25.61፣ 78.13፡፡ ፀሐይ የራሷን ዙሪያ ትዞርና ወደ ማረፊያዋ ቦታ ትሄዳለች 36.40፣ 18.86)፡፡ ፀሐይ ከጨረቃ ጋር እንድትወዳደር አይፈቀድላትም እንዲሁም ጨረቃ ፀሐይን እንድተቀድም አይፈቀድላትም እያንዳንዳቸውም በተመደበላቸው መስመር ብቻ ነው የሚሄዱት 36.37-40፣ 21.32-33፡፡ አላህ በፀሐይ በብርሃኗ በጨረቃም ምሏል 91.1-2፡፡

አዳምና ሔዋን፡- አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት በሰማይ ባለው የገነት አትክልት ቦታ ነው፡፡ ከሰይጣን በቀር መላእክት ሁሉ ለአዳም በመስገድ አላህን ታዘዋል፡፡ ሰይጣን ባለመታዘዙ የተነሳ ለዘላለም ተሽሯል፡፡ ሰይጣንም በበኩሉ አላህ እንዳይቀርቧት ካዘዘው ዛፍ እንዲበሉ አዳምንና ሔዋንን ፈተናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ከሰማያዊቷ የአትክልት ቦታ አዳምንና ሔዋንን አላህ አስወጣቸው እና በምድር ላይ አስቀመጣቸው 7.11-25፡፡

ልዩ የሆነው ሰው፡- ሁሉን ነገርን ለማድረግ የሚችል ታላቅ ሰው ተፈጥሮ ነበር፡፡ ስሙም ዙልቀርነይን የተባለ ነው፡፡ እሱም ወደ ሩቅ ምዕራብ ተጉዞ ፀሐይ ጥቁር ጭቃ ውስጥ ስትጠልቅ አያት፡፡ እዚያም ባሉ ሰዎች ላይ እንዲገዛ ስልጣን ተሰጠው በኃይልም ገዛቸው፡፡ ደግሞም እንደገና በሌላ መንገድ እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ ተጓዘ እዚያም ለፀሐይ መውጪያ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች አየ፡፡ እነሱም በጣም ከሚያቃጥለው የቀረበ የፀሐይ ብርሃን ኃይል መቃጠል የሚጠብቃቸው ማንም አልነበረም፡፡ እነዚያንም ሰዎች ብቻቸውን ተዋቸው፡፡ ሌላው እሱ ያደረገው ነገር ከብረት ቁራጮች ትልቅን ግድብ መስራትና በቀለጠ ነሐስም መሸፈን ነበር፡፡ እሱም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በሁለት ተራራዎች መካከል ያለውን ክፍት ቦታ ሞልቶት ነበር፡፡ ይህም የጎግ ማጎግ የተባሉት ሕዝቦች እንዳይደርሱበትና ጎረቤቶቻቸውን እንዳይረብሹ ነው፡፡ ይህም ታላቅ ግድብ እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ ይኖራል 18.83-100፡፡

የወንድ ዘር ፈሳሽ፡- የምታፈሱትን ዘር ታያላችሁን? እናንተ ፈጥራችሁታልን ወይንስ እኛ ነን የፈጠርነው? 56.58-59፡፡ ሴትና ወንድን ከፍትወት ጠብታ ፍሳሽ ፈጠረ 53.45-46፡፡

ወፎች፡- ወፎች በሰማይና በምድር መካከል ለመንጠልጠላቸው ምንም ዓይነት ሰዋዊ መግለጫ ስለማይኖር እምነትን ለማሳየት ምልክት ናቸው፡፡ ይህም በአላህ ተዓምራታዊ ኃይል የሆነ ነው 16.79፡፡

ጥላ፡- ጥላዎችን የሚያስረዝማቸውና የሚያሳጥራቸው አላህ ነው፡፡ እነሱንም በአንድ ቦታ የቆሙ ሊያደርጋቸው ይችል ነበር፡፡ እነሱንም የምትመራቸው ፀሐይ ናት 25.45፡፡

ዙፋን፡- ሰማያት ተሰርተው ከተፈፀሙ በኋላ እነሱን የገነባቸው አላህ በሰማይ ዙፋኑ ላይ ለመቀመጥ ሄደ (10.3፣ 13.2፣ 20.5፣ 25.59፣ 57.4)፡፡ አላህም ሰማይና ምድር እንዳይጠፉም እነሱን መያዙን ቀጠለ 35.41:: የአላህን ዙፋን ደግፈው የያዙትና የተሸከሙት፣ ምህረት የሚገባቸው ሙስሊሞች  ምህረትን እንዲያገኙ ያለማቋረጥ ይፀልያሉ 40.7-9፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሙስሊሞች ሲናገሩ የሚሰማው ቁርአን ከእግዚአብሔር ለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ የሚሆነው ምንም ስህተት የሌለው ሳይንሳዊነቱ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ በላይ በM.J Fisher, M.DIV በጥንቃቄ ተለቅመው የቀረቡት የቁርአን ጥቅሶች የሚያስረዱት ግን ተፃራሪውን ነው፡፡ ቁርአን በሳይንስ ሊረጋገጥ የሚችል ምንም ተጨባጭ ነገር የለውም፡፡ ስለዚህም ቁርኣን ሳይንሳዊ ናቸው በማለት ያቀረባቸው ነገሮች ሁሉ ሳይንስ አለመሆናቸው መጽሐፉ ከእግዚአብሔር ላለመሆኑ እውነተኛ ማረጋገጫ ነው፡፡

እንግዲህ እግዚአብሔርን ለመከተል የሚፈልግ ማንም ሰው ቢኖር ከእግዚአብሔር ባልሆነ መጽሐፍ ላይ ሊመራና ሊታመን አይገባውም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ፈቃድና ዕቅድ እንዲሁም እውነታውን ሊያውቅ አይችልምና፡፡

ስለዚህ አንባቢዎችን የምንመክረው ሳይንሳዊም፣ ታሪካዊም፣ ስነጽሑፋዊም ሆነ ማንኛውም ቅንጣት ስህተት ወደ ሌለበት ወደ እግዚአብሔር ቃል ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በመምጣት ለራሳችሁ እንድታነቡት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ ከምታገኙዋቸው አስደናቂ ነገሮች ውስጥ አንዱ ስለ ሰው ልጅ ኃጢአተኝነትነው፡፡ ሰው በኃጢአተኝነቱ ከእግዚአብሔር እንደራቀ የቅዱስ እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቀው ነው፡፡ ነገር ግን በምህረቱ ወደር የሌለው እግዚአብሔር ለዚህ የሰው ልጆች ጥልቅ ችግር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያቀርበው መፍትሔ ሌላው አስደናቂና ግሩም እውነት ነው፡፡ ይህም የምስራች ዜና ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡

ኃጢአተኛው ሰው ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና መንግሰተ ሰማይን መውረስ እንዲችል እግዚአብሔር አስደናቂ መንገድን አዘጋጀ፣ አስደናቂ መግቢያ በርን ከፈተ ይህም የሚቻለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህም በቅዱስ እግዚአብሔር ዙፋን ፊት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመቅረብ ንስሐ የሚገቡና የኃጢአታቸውን ይቅርታ ከእግዚአብሔር የሚለምኑ ሁሉ ስለ ጌታ ኢየሱስ ይቅር ተብለው አዲስ ሕይወትን ይቀበላሉ፡፡ የእግዚአብሔርም ልጆች ተብለው ይቆጠራሉ የዘላለምም መንግስት ወራሾች ይሆናሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን እውነት በዝርዝር ያስረዳል አግኙት በዝግታ አንብቡትና መልእክቱን በጥንቃቄ ተረዱ፡፡ የምህረቱ አምላክ እግዚአብሔር እውነቱን እንድትገነዘቡ ለማድረግ በቅዱስ መንፈሱ እንዲረዳችሁ ፀሎታችን ነው፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Creation and Science, Chapter 7 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ